አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከስዊዝ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር የሶፍትዌር ልማት ስምምነት ተፈራረመ

178
አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ስራዎችን የሚመዘግብ ሶፍትዌር ለማልማት ከስዊዝ የፌደራል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት ተፈራረመ። ቴክኖሎጂው የምርምር ውጤቶችን እየመዘገበ በአንድ ቋት ይዞ የሚያቆይ እና ሲፈለጉም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ሶፍትዌር ነው። በሂደት ላይ ያሉ የጥናት ሥራዎችን ርእሰ ጉዳዮችና የደረሱበትን ደረጃ የተመለከቱ መረጃዎችን በመጠቆም የክትትል ተግባራትን ለማከናወንም ያግዛል። ቴክኖሎጂው በስራ ፈጠራ የተሻለ የቢዝነስ እቅድ የሚያቀርቡ ወጣት ተመራማሪዎችን በመለየት ለማበረታታት ይቻል ዘንድ ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል ተብሏል። የሶፍትዌር ቴክኖሎጂው የሚሰራው መቀመጫው በስዊዘርላንድ ፌደራል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በድጋፍ መልክ ነው። ሶፍትዌሩን መስራት የሚያስችለው የድጋፍ ስምምነት ዛሬ በአዲስ አበባ የተፈረመ ሲሆን የሶፈትዌር ሥራው እስከ 600 ሺህ ዶላር ሲፈጅ በየዓመቱ ለሚካሄደው የጥገና ሥራ ደግሞ ከ20 ሺህ ዶላር በላይ ወጪ ይደረጋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው ካሁን በፌት የነበረው ሶፍትዌር የምርምር ስራዎች በአገሪቱ ላይ ምን ለውጥ አመጡ? በቀጣይ እንዴት ይሰራባቸው? የሚሉና ሌሎች መረጃዎችን የሚይዝ አልነበረም ብለዋል። አዲሱ ቴክኖሎጂ ግን በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ የምርምር ስራዎች ከመደርደሪያ ባለፈ ሀገራዊ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ያግዛል ሲሉም ገልፀዋል። ለባለሙያዎች ስልጠና ከተሰጠ በኋላ ቴክኖሎጂው ሥራ ላይ የሚውል መሆኑንም የዩኒቨርሰቲው ፕሬዝዳንት ተናገረዋል። የሶፍትዌር ግንባታውን የሚያከናውነው የስዊዝ ፌደራል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሻለ ልምድ ያለው በመሆኑ በጥናትና ምርምሮች ላይ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር እንደሚያግዝም ገልጸዋል። በስዊዘርላንድ የተስፋ ኢልግ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንትና የስዊዝ ፌደራል ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተወካይ አቶ ዳዊት ተስፋዬ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚበረከተው ቴክኖሎጂ ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ በጋራ ለመስራት በማለም መሆኑን አስታውቀዋል። አቶ ዳዊት እንዳሉት ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የምርምር ስራዎች በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ከማድረግ ባሻገር ለህብረተሰቡም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛልም ብለዋል። የተሻለ የቢዝነስ እቅድ የሚያቀርቡ ወጣት ተመራማሪዎችን ለመለየትና ማበረታታት የሚያስችል መሆኑን የተናገሩተ አቶ ዳዊት ድርጅታቸው የተሻለ የቢዝነስ እቅድ ለሚያዘጋጁ ወጣቶች እውቅናና ሽልማት ይሰጣል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም