በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ቀረበ

68
አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2010 በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኢትዮጵያዊነት ከልባቸው ከቶ ሊጠፋ እንደማይችል ያስመሰከሩባቸውን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግስት ጥሪ አቀረበ፡፡ የተጀመረው የአንድነትና የመደመር የለውጥ እንቅስቃሴ በአጭር ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ መጠነ ሰፊ፣ ተከታታይና ፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጣዊ አንድነታችንን ከማጠናከር በላይ ኢትዮጵያ በአለም የሚሰጣትን ግምት ያሳደገ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ አስታውቋል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በቅርቡ በተከፈተው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ማበርከት የጀመሩት አስተዋጽኦ ከገንዘብ ድጋፍ በላይ የሚታይ ፍፁም አገር ወዳድነትና የለውጥ ደጋፊነት የተንፀባረቀበት መሆኑን ፅህፈት ቤቱ ገልጿል። ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያኑ ቴክኖሎጂንና ዕውቀትን በማሸጋገር፣ በአገራቸው ኢንቨስት በማድረግና የሌሎች አገሮችን ኢንቨስተሮች በመሳብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲያግዙ ፅህፈት ቤቱ በመግለጫው ጠይቋል። የቱሪዝም መስህቦችንና ምርቶችን ለዓለም በማስተዋወቅና በመሳሰሉ ሌሎች ታላላቅ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ተግባራት ላይ በመሰማራት የተሻለች ኢትዮጵያ ለመፍጠር እየተካሄደ ያለውን ጥረት እንዲያግዙም መንግሥት ጥሪውን አስተላልፏል። በለውጡ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በአገሪቱ ላይ መተማመን እንዲፈጠርባቸውና በዓለም መድረክ ባለው ውድድር ውስጥ ለአገሪቱ የሚሰጡትን ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጓል ተብሏል። ከጎረቤት አገሮች ጋር በፍቅርና በመደመር ስሌት በተወሰዱ እርምጃዎች መልካም ጉርብትናና ትስስርን በማጥበቅ ለጋራ ዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር እንዲሁም ለክፍለ አህጉሩ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደተቻለም ጠቁሟል። የተለያየ አመለካከት በማራመድ እርስ በርስ በጥላቻ ሲተያዩ የነበሩ ወገኖች ያለፈውን ቂምና ጥላቻ ረስተው በይቅርባይነትና በፍቅር ከውጭም፣ ከውስጥም በአንድነት በመሰባሰብ ለአገር ግንባታ በጋራ መስራት ላይ መሆናቸው ተገልጿል። ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለቅ ቀርቧል በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር ጉዞ የተሻለች አገር ለመፍጠር እንረባረብ በፍቅር፣ አንድነትና መደመር ጉዞ ላይ ሆነን በአጭር ጊዜ ውስጥ ባከናወናቸው መጠነ ሰፊ፣ ተከታታይና ፈጣን የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር ላይ እንገኛለን። ትናንት ልባችን ተራርቆ የነበርን የአንዲት እናት ልጆች ዛሬ በይቅርታና በፍቅር ተሳስረን በጋራ መስራት በመቻላችን ከወዲሁ ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማየት ጀምረናል፡፡ ከአጎራባች አገራት ጋር በፍቅርና በመደመር ስሌት በወሰድናቸው እርምጃዎች መልካም ጉርብትና እና ትስስርን በማጥበቅ ለጋራ ዘላቂ ሰላምና ልማት መጠናከር ጥሩ መደላድል ከመፍጠራችንም በላይ ለምንገኝበት ክፍለ አህጉር ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና መረጋገጥ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት ችለናል፡፡ የተያያዝነው የፍቅር፣ የአንድነትና የመደመር የለውጥ እንቅስቃሴ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የነበረንን አስከፊ ገጽታ በመቀየር አገራት እና ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች በአገራችን ላይ መተማመን እንዲፈጠርባቸው እና በዓለም አቀፉ ውድድር ውስጥ ለአገራችን የሚሰጡትን ዋጋ ከፍ እንዲል ማድረግ አስችሎናል። የገንዘባችንን የመግዛት አቅም ማጠናከር፣ ከወዳጅ አገራት እና ተቋማት የምናገኘውን ድጋፍ ማሳደግን የመሳሰሉ ሌሎች ውጤቶችንም በማስመዝገብ ላይ እንገኛለን፡፡ሁሉ በላይ ደግሞ የተለያየ አመለካከት በማራመዳቸው ብቻ ትናንት እርስ በርስ በጥላቻ ሲተያዩ የነበሩ ወገኖቻችን ያለፈውን ቂም እና ጥላቻ ረስተው በይቅርባይነት፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመደመር ጉዞ ከውጭም፣ ከውስጥም በአንድነት በመሰባሰብ ለአገር ግንባታ በጋራ እየሰሩ ያሉበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ በተለይም፣ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል ቀደም ባለው ጊዜ በትጥቅ ትግል ጭምር ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አመራሮች ወደ አገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለአገራቸው አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታ መፈጠሩ ታላቅ ስኬት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በውጭ የሚኖረው እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከሻይና ማኪያቶ ቀንሰው በቀን አንድ ዶላር ገቢ እንዲያደርጉ  ያቀረቡትን ጥሪ በመቀበል እየሰጡት ያለው ፈጣን እና ተስፋ ሰጪ ምላሽም ሌላው ምስጋና የሚገባው ተግባር ነው። ኢትዮጵያውያኑ በተከፈተላቸው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ለአገራችን ማበርከት የጀመሩት አስተዋጽኦ ከገንዘብ ድጋፍ በላይ የሚታይ ፍፁም አገር ወዳድነትና የለውጥ ደጋፊነት የተንፀባረቀበት ተግባር ነው። ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ያሳዩት ይኸው ተነሳሽነት እኛ ኢትዮያውያን ጥላቻን በማስወገድ በፍቅር፣ በአንድነት እና በመደመር በጋራ እስከተንቀሳቀስን ድረስ አሁን ያለው ትውልድ የራሱን ታሪክ በመስራት የተሻለች አገር መፍጠር እንደሚችል ለተጨማሪ አገር ወዳድ ስራዎች የማንቂያ ደውል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ በመሆኑም የኢፌዴሪ መንግስት ምስጋናውን ለማቅረብ ይወዳል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ወጥተው በዬትኛውም የዓለም ጥግ ይኑሩ እንጂ ኢትዮጵያዊነት ከልባቸው ከቶ ሊጠፋ እንደማይችል ያስመሰከሩባቸውን ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ቴክኖሎጂንና ዕውቀትን በማሸጋገር፣ በአገራቸው ኢንቨስት በማድረግ እና የሌሎች አገራትን ኢንቨስተሮች ወደ አገራችን በመሳብ፣ የቱሪዝም መስህቦቻችንን እና ምርቶቻችንን ለዓለም በማስተዋወቅ እና በመሳሰሉ ሌሎች ታላላቅ አገራዊ ፋይዳ ባላቸው ተግባራት ላይ በመሰማራት የተሻለች አገር ለመፍጠር እየተካሄደ ያለውን ጥረት እንዲያግዙም መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም