የትግራይ ክልልን የልማት ለውጦች ዘላቂ ለማድረግ በምርምርና ጥናት ማጠናከር ያስፈልጋል---ምሁራን

88
መቀሌ ሀምሌ 13/2010 በክልሉ እየታዩ ያሉት ተጨባጭ የሆኑ የልማት ለውጦችን ዘላቂ ለማድረግ የምርምርና ጥናት ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የትግራይ ተወላጅ ምሁራን ገለጹ፡፡ በመቀሌ እየተካሄደ ባለው የትግራይ ክልል ተወላጅ ምሁራን ዓለም አቀፍ ኮንፈረስ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ምሁራን እንዳሉት፣የክልሉን ችግሮች ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች እንዲጠናከሩ መንግስት ከእነሱ ጋር  የጀመረውን መቀራረብ አድንቀዋል። ከምሁራኑ መካከል በስዊዲን የሶፍትዌር ከፍተኛ ባለሙያ ኢንጂነር ንግስቲ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት ኮንፈረንሱ በሀገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅና ክልሉንም  በሙያቸው ለማገዝ የሚችሉበት ግንዛቤ እንዲያገኙ የረዳቸው መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መሰራት ስላለባቸውና  በአሁኑ ወቅት ያለበትን ችግር እየተጠና መሆኑን ከኮንፈረንሱ መገንዘብ እንደቻሉም አመልክተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ መጥተው በኮንፈረንሱ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ዶክተር ብርሃኑ ገብረመድህን በበኩላቸው፣  የልማት ውጤት  የአንድ አካል ብቻ ሳይሆን በምርምርና ጥናት የተደገፈ የምሁራን ሁለንተናዊ አቅም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። ዶክተር ብርሃኑ እንዳመለከቱት ከኮንፈረንሱ የሚገኙ የተለያዩ ግብአቶችን ለፖሊሲና ስትራቴጂ አውጪዎች በሚያግዝ መልክ መዘጋጀትና በምርምር ሊደገፉ ይገባል፡፡ ያለ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ያለሙከራ የሚከናወኑ ስራዎች ውድቀታቸውም ሆነ ስኬታቸው ለመለካት እንደማይቻል የገለጹት ደግሞ አሜሪካ ከሚገኘው አለምአቀፍ የምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት የመጡት ዶክተር ሆስእና ገብሩ ናቸው። እንደሳቸው ገለጻ፣ጥናትና ምርምር በሀገሪቱ ለሚካሄዱ ስራዎች ዘላቂነት ወሳኝ ነው። ከእንግሊዝ ሸፊልድ ከተማ የመጡት ፕሮፌሰር ሰሎሞን ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት ፣ላለፉት 18 ዓመታት ከጥቁር አንበሳና ጦር ኃይሎች ሆስፒታሎችን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከውጭ ባለሙያዎች ጋር በማገናኘት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ተናግረዋል። በክልሉ እየታዩ ያሉት ተጨባጭ የሆኑ የልማት እንቅስቃሴዎችና ለውጦችን  ዘላቂነት እንዲኖራቸው በጥናትና ምርምር ስራዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም ምሁራኑ አመልክተዋል። እስካሁን በኮንፈረንሱ የትግራይ ክልል ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ትምህርትና በጤና ዘርፎች የሚታዩ ክፍተቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን የሚዳስሱ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በቀጣዮቹ ቀናትም በግብርናና ሌሎች ዘርፎች በሚቀርቡ ጥናቶች ላይ ምሁራኑ የጋራ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ የትግራይ ክልል ተወላጅ ከፍተኛ ምሁራን የተሳተፉበት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ሐምሌ 11/2010ዓ.ም በመቀሌ ከተማ  እንደተጀመረ ይታወቃል  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም