በኢትዮጵያ 60 በመቶ የሚሆኑ ህጻናት በትምህርት ቤቶች አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው አንድ ጥናት አመለከተ

104

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ህጻናት በትምህርት ቤቶች ውስጥ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው አንድ ጥናት አመላከተ።

አለም አቀፉ የስርአተ ጾታና የወጣቶች መረጃ ፕሮግራም (ጌጅ) አለም አቀፍ የሪሰርች ፕሮግራም በኢትዮጵያ በሴቶች፣ ታዳጊ ህጻናትና ወጣቶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት ይፋ አድርጓል።

በፕሮግራሙ አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር አስተባባሪ አቶ ወርቅነህ አበበ ጥናቱ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን፣ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሃረርጌ ዞን፣ በአፋር ክልል ዞን 5 እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር አካባቢዎች ላይ የተካሄደ የረዥም ጊዜ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል።   

እድሜና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲሁም የታዳጊዎች ጤናና ደህንነት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንም አክለዋል።

በዚህ በጥናቱ ግኝት መሰረት ታዳጊዎች በአብዛኛው በቤተሰቦቻቸው፣ በትምህርት ቤቶች እና በማህብረሰቡ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በእነዚህ አካባቢዎች ላይ በተደረገው ጥናትም 50 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ህጻናት በቤተሰቦቻቸው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሲሆን ከ29 እስከ 60 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ህጻናት ደግሞ በትምህርት ቤት በመምህራኖቻቸው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን አመላክተዋል።

አብዛኞቹ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ታዳጊ ህጻናት እድሜያቸው ከ10 እስከ 14 የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአካባቢዎቹ ላይ በተደረገው ጥናት ወደ 47 በመቶ የሚሆኑ ታዳጊ ልጃገረዶች ግርዛት እንዲሁም 50 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባቸው መሆኑንም ነው ያመላከቱት።

በዚህም ከፍተኛ የፖሊሲ አቅጣጫ በማስቀመጥና በመተግበር፣ መምህራን ተማሪዎችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ በስነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም የስነ-ተዋልዶ ጤናን ታዳጊዎች ጋር በማድረስ ረገድ ጠንካራ ስራ መሰራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር የታዳጊዎች ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም፤ መንግስት የወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባና አመርቂ ውጤት ማምጣት እንዳለበት ይገነዘባል።

ላለፉት 10 አመታት ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ በተዋልዶ ጤና፣ በኤች አይ ቪ፣ በስርአተ-ምግብ እንዲሁም ከአደጋ ጋር ተያይዞ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ስርታቴጂዎች ተቀርጸው በስራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ከክልል ጤና ቢሮ ሃላፊዎችና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆንም በወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና ተደራሽነት አንጻር ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለማስፋፋትና የጤና መረጃ አገልግሎትም እንዲያገኙ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛት ያሉ ጎጂ ልማዳዊና ባህላዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የአምስት አመት ፍኖተ ካርታ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሰዋል።

ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ጥምረት ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሴቶችና የህጻናትን ደህንነት ለማሻሻል እንዲሁም የስርአተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚገጥሙ ችግሮችን መነሻቸው፣ የሚያስከትሉት ጉዳትና መፍትሄዎቻቸውን መለየት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የጥናትና ምርምር ተቋማት አጋዥ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማድረግ ተከታታይ እገዛ ማድረግ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

በዚህም የትኛዋም ታዳጊ ሴት ወደ ኋላ እንዳትቀር ብሎም ማንኛቸውም እድሜና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውም መወጣት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም