በታንዛኒያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ሐብት እየተሰባሰበ ነው - አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ

50

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 13/2013 ( ኢዜአ) በታንዛኒያ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ሐብት እየተሰባሰበ መሆኑን በአገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ ገለጹ። 

በአገሪቷ አራት እስር ቤቶች ከ1 ሺህ 100 በላይ ኢትዮጵያዊያን በእስር ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

በታንዛኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ችግር ለማቃለል ማረሚያ ቤቶቹን መጎብኘታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዳሬሰላም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረቦች ካለፈው ሕዳር መጨረሻ ጀምሮ እስካለፈው ሳምንት ድረስ በታንጋ፣ በሞሮጎሮ፣ በባጋሞዮና ፕዋኒ ግዛቶች በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ዜጎችን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝቱ ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር በነበረ ውይይት በደላሎች ተታለው ለስቃይና ለእንግልት ተዳርገው ወደ አገሪቷ መግባታቸውን ገልጸዋል።

በታንዛኒያ በሚገኘው የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት /አይ.ኦ.ኤም/ የሕክምና ቡድን አማካኝነት የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

የምግብና ሌሎች ሰብዓዊ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ኤምባሲው ዜጎቹ ያሉበትን ሁኔታ በተለይም የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን በቅርበት በመከታተል ላይ እንደሚገኝ አምባሳደር ዮናስ ተናግረዋል።

ከታንዛኒያ የአገር ውስጥ ጉዳይና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ዜጎቹ ተፈተው ወደ አገራቸው በሚመለሱበት ሁኔታ ላይ ውይይትና ድርድር እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም ባለሥልጣናቱ ዜጎቹ ተፈተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ፈቃደኝት አሳይተዋል ነው ያሉት።

በእስር ቤቶቹ የሚገኙትን ዜጎች ለአገራቸው ለማብቃት ከፍተኛ ገንዘብ ያስፈልጋል ያሉት አምባሳደር ዮናስ፤ ለዚህም የሀብት ማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት /አይ.ኦ.ኤም/ን ጨምሮ ከሌሎችም አጋሮች የሚያስፈልገው ገንዘብ ሲሟላ  ዜጎቹን ወደ አገራቸው መመለስ ይጀመራል ብለዋል።

በቀጣዩ ወር በአገሪቷ ሌሎች ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ የማየትና ተጓዳኝ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ነው አምባሳደር ዮናስ ያብራሩት።

ወደ ታንዛኒያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያዊያን ደቡብ አፍሪካን መዳረሻቸው አድርገው እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል።

"ወደ ታንዛኒያ የሚሰደዱት ኢትዮጵያዊያኑ ለደላሎች ከሶስት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ዶላር ይከፍላሉ" ብለዋል አምባሳደር ዮናስ።

ይህን ገንዘብ በሚኖሩበት አካባቢ ሥራ ቢፈጥሩበት ኑሯቸው እንደሚሻሻል በመጠቆም።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ዜጎች በአገራቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ በማስረዳት የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም አመልክተዋል።

ኤምባሲው በተያዘው የአውሮጳዊያን ዓመት በእስር ላይ የነበሩ 1 ሺህ 600 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መልሷል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በዳሬሰላም የተከፈተው ኤምባሲ ከ3 ሺህ 100 በላይ ዜጎችን ከእስር አስፈትቶ ወደ አገር ቤት መመለሱንም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም