ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ መነፅር ማድረግ የዓይን ህመምን ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋገር ይችላል- የጤና ባለሙያዎች

227

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 12/2013 (ኢዜአ) ከሃኪም ትእዛዝ ውጭ መነፅር ማድረግ በህክምና ሊድን የሚችል የዓይን ህመምን ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋገር ስለሚችል ማህበረሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት የጤና ባለሙያዎች አሳሰቡ።

የአይን ሕክምና ባለሙያዎች ሰዎች የአይን መነጽር ሲጠቀሙ ባለሙያዎችን ማማከር እንደሚገባቸውና የሚጠቀሙበት መነጽር ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ይመክራሉ።

ደረጃውን ያልጠበቀ የአይን መነጽርን እንዲሁም የአይን መነጽርን ያለ ሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ መጠቀም የአይን መንሸዋረር፣ ደብዛዛ እይታና ራስን የማዞርና ከፍተኛ የራስ ምታት ስሜት እንደሚያስከትል ነው የአይን ሕክምና ባለሙያዎች የሚገልጹት።

በተጨማሪም አይንን ማሳከክና ማቃጠል፣ የአይን ቆብ መዛልና በረጅም ጊዜ በአይን ላይ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ደረጃውን ያልጠበቀ የአይን መነጽር እንዲሁም የአይን መነጽርን ያለ ሕክምና ባለሙያ ትዕዛዝ መጠቀም የሚያመጣቸው የሕመም ስሜቶች የተለያዩ የጤና ችግሮችን እንደሚያመጣም ነው ባለሙያዎቹ የሚያስረዱት።

ሰዎች ያለባቸውን የአይን እይታ ችግር ለአይን ሕክምና ባለሙያዎች በዝርዝር ማስረዳት እንዳላባቸው ለእይታቸው የሚሆን መነጽር እንዲያዙላቸው ቢያደርጉ መልካም እንደሆነ ይነገራል።

በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡን በስፋት እያጠቁ ከሚገኙ የጤና ችግሮች መካከል የዓይን ሕመም አንዱ መሆኑም ይነገራል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የዓይን ሕክምና ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ደረጄ ሃይሉ እንደሚሉት አብዛኛው የዓይን ህመም በመታከምና በሃኪም ትእዛዝ በሚደረግ መነፅር መስተካከል የሚችል ነው።

“ህብረተሰቡ ዓይኑን ከአቧራ፣ ከጸሐይና መሰል ድርጊቶች ለመጠበቅ በሚል የሕክምና ባለሙያዎችን ሳያማክርና ሳይመረመር የሚያደርጋቸው መነፅሮች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው ያመዝናል” ብለዋል፡፡

በሃኪም ትእዛዝ ለአይን ተስማሚና ትክክለኛ መነፅር ባለመጠቀም ምክንያት በቀላሉ ሊድን የሚችል የዓይን ህመም ወደ ከፋ ደረጃ እንደሚሸጋገርም ነው የጠቆሙት።

“መነፅር መድኃኒት ነው፤ እንደማንኛውም ሸቀጥ በየቦታው መሸጥ የለበትም” ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ።የዓይን መነጽሮችን በባለሙያ ትዕዛዝ መጠቀም የዓይንን መድከም በመቀነስና ከዓይነ ስውርነት ይታደጋልም ብለዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በዓይን ሕክምና ትምህርት ክፍል ኬዝ ቲም አስተባባሪ እፀገነት ብርሀኔ፤ ህብረተሰቡ የዓይኑን ደህንነት በየጊዜው በመከታተል ጤናውን መጠበቅ እንዳለበት ይናገራሉ።

በተለይ እንደ ሞባይልና ኮምፒውተር ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ላይ ለረጅም ሰዓት ከመቆየት መቆጠብ የአይንን ጤንነት ለመጠበቅ መፍትሄ መሆኑን ይመክራሉ።

በርካታ ሰዎች የዓይን ህመም ሲገጥማቸው ያለ ሃኪም ትእዛዝ መነፅር እንደሚያደርጉ የጠቀሱት ባለሙያዋ ድርጊቱ ትክክል አለመሆኑን አብራርተዋል።

ለፀሐይ ብርሃንና ለአቧራ መከላከያ ሊውሉ የሚችሉ መነጽሮችንም በጤና ባለሙያ ምክርና እገዛ ብቻ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም