ከታህሳስ 23 ጀምሮ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ወደ ኢትዮሳት ይዞራሉ

3513

ታህሳስ 12 /2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሚገኙ የቲቪ ተመልካቾች ከታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ጀመሮ አብዛኛዎቹን የአገር ውስጥ ጣቢያዎች በኢትዮሳት 57 ዲግሪ ምስራቅ በብቸኝነት መከታተል እንደሚችሉ ተገልጿል።

ተመልካቾቹ የሳተላይት አንቴናቸውን አቅጣጫ በሚገባ በማስተካከል ፕሮግራሞቹን መከታተል ይችላሉ ተብሏል፡፡

ለዚህ ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት (የመንግስትና የግል ቴሌዥን ጣቢያዎችን በመወከል) እና ኤስ ኢ ኤስ የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ ሁሉንም የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ወደ አንድ ማዕከል በማካተት ለተመልካቾች አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው ተብሏል፡፡

ኢትዮሳት በነጻ አየር ላይ የዋለ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የሳተላይት ቴሌቪዥን መደላድል መሆኑም ተገልጿል፡፡

ጣቢያውን ተደራሽ ለማድረግ ለ20 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ስልጠና በመስጠት የመቀበያ ሳህኑንና አቅጣጫውን እንዲያስተካክሉ ይደረጋል፡ ፡

ኢትዮሳትን መግጠም የሚፈልጉ ተመልካቾች የመቀበያ ሳህኑን ወይም ዲሹን አቅጣጫ በማዞር መጠቀም የሚችሉ ሲሆን ስልጠና የወሰዱትን ባለሙያዎች በማነጋገርም ማስተካከል ይችላሉ ተብሏል፡፡

አዲስ ቴሌቪዥንም ሆነ ዲሽ መግዛት አይጠበቅባቸውም ነው የተባለው፡፡

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ “በርካታ የኢትዮጵያ የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ወደ አንድ ማዕከል ማምጣቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሚገባ ይጠቅማል፣ ከዚህ ባለፈ የቴሌቪዥን ጣቢያ ማህበርና ኤስ ኢ ኤስ በጋራ በመሆን በመላ አገሪቱ የሚገኙ ተመልካቾ ጥራት ያለው ምስል እንዲያገኙ ለማስቻል ይሰራሉ” ብለዋል።

“በኢትዮጵያ አዲስ የሆነውን የቴሌቪዥን አገልግሎት ከኤስ ኢ ኤስ ጋር በመሆን በኢትዮሳት አማካኝነት ለኢትዮጵያውያን እንዲደርስ ማድረጋችንን ስንገለጽ ደስታ ይሰማናል” በማለት የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖለጂ ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ ተናግረዋል፡፡

“ትብብሩ በኢትዮጵያ ያለውን የስፔስ ዘርፍ ለማሳደግ የተያዘውን ቁርጠኝነት ከማሳየቱ በላይ ለአገሪቱ የሚዲያ ዘርፍ መጻኢ እድገት አዲስ መደላደልም ይፈጥራል” ብለዋል፡፡

የኤስ ኢ ኤስ ዋና ተጠሪ ስቲቭ ኮላር በዚህ ልዩ ፕሮጀክት በመሳተፋቸው ኩራት እንደሚሰማቸውና ኢትዮሳት ጥራት ያለውና ተመልካቾቹን የሚያረካ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮሳት አሁን ላይ 65 የቴሌቪዥን ቻናሎችን የተቀበለ ሲሆን ከነዚህ መካከል 16ቱ በሀይ ዴፊኒሽን (HD) ጥራት የሚሰሩ ሲሆን ከታህሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ጀመሮ አየር ላይ ይውላሉ ተብሏል፡፡