የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በውቅሮ ከተማ ከነዋሪዎች ጋር ተወያየ

105

አዲስ አበባ ታህሳስ 12/2013 (ኢዜአ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ከውቅሮ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ በመሩት የውይይት መድረክ በርካታ የውቅሮ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱም የኤሌክትሪክ፣ የውሃ ችግርና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ችግር መንግስት በአጭር ጊዜ እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል።

ነዋሪዎቹ አሁንም ከቴሌ ኮሙኒኬሽን፣ ከባንክ፣ ከህክምና እንዲሁም ከትራንስፖርት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ችግሮች እንዳሉባቸው ተናግረዋል፡፡ 

የመከላከያ ሠራዊቱ ውቅሮ ከተማ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

በቀጣይም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በአፋጣኝ መዋቅሩን በመዘርጋት የህዝቡን ደህንነት ማስጠበቅና የመልሶ ግንባታ ሥራ ሊጀምር ይገባል ብለዋል። 

በተለያዩ አጋጣሚዎች የጦር መሳሪያ የታጠቁ ግለሰቦችም ለመንግስት ማስረከብ አለባቸው ብለዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ፣ ህብረተሰቡ ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ ያነሳቸው ጥያቄዎች በአፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን አመራሮች በራሱ ፈቃድ ነጻ ሆኖ እንዲመርጥ ለማድርግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ፤ የትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማቱን ለማረጋገጥ በጋራ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

የወደሙ መሰረተ ልመቶችን መልሶ ለመገንባት ርብርብ በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸው ህዝቡ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በውቅሮ ከተማ ጊዜያዊ የአስተዳደር መዋቅር የመዘርጋት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም