ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ሦስት ሳተላይቶችን ታመጥቃለች

57

ታህሳስ 11/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ለተለያየ አገልግሎቶች የሚውሉ ሦስት ሳተላይቶችን እንደምታመጥቅ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደገለፁት፤ በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ሦስት ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ታቅዷል።

በአሥር ዓመቱ ከሚመጥቁት ሳተላይቶች ውስጥ አንደኛው የኮሚዩንኬሽን እና ብሮድካስት ሲሆን፤ የተቀሩት ሁለቱ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ናቸው።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የኮሚዩንኬሽን እና ብሮድካስት ሳተላይት የሚባለው በብሮድካስት ሚዲያዎች ለኢንተርኔት፣ ለስልክና ለኮሚዩንኬሽን አገልግሎት የሚውል ነው።

በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን እነዚህን አገልግሎቶች ከውጭ በመከራየት በሚሊዮን ዶላር የሚገመት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታወጣለች።

ለአብነትም፣ ከብሮድካስቲንግ በዓመት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረጋል እንደ ኢፕድ ዘገባ።

ለቴሌ ኮሚዩንኬሽን ደግሞ በርካታ ሚሊዮን ዶላሮች ወጭ ይሆናሉ።

ስለዚህ ሳተላይት የመገንባት እቅዱን በተግባር በማረጋገጥ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ ተገቢ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም