በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና የሰላም ሂደት የህዝቡ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩና የመንግሥት ትብብር ያስፈልጋል-- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ

58

አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል መልሶ ግንባታና የሰላም ሂደት የህዝቡ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ የፌዴራሉ መንግሥትና የመከላከያ ሠራዊት ትብብር ወሳኝ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ገለጸ።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ በትግራይ ክልል በሚያደርገው የመስክ ምልከታ በቁጥጥር ስር ያሉ እስረኞችን፣ የተፈናቀሉ ዜጎችንና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመጎብኘት ከማህበረሰቡም ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል።

መርማሪ ቦርዱ በመልሶ ግንባታና የሰላም ሂደት እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችንና ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ በሽሬ ከተማ ከጊዜያዊ አስተዳደሩና ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱም የሽሬ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ገብረ ፃዲቅ፣ የህግ ማስከበሩ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ  የተወሰዱ ንብረቶችን የማስመለስ፣ ህዝቡን የማረጋጋትና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲመለሱ የማድረግ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በየኬላው ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን በጸጥታ ስጋት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እንዲመለሱና ድጋፍ እንዲያገኙም እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የህወሓት ጁንታ ውድመት ካደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች መካከል የመብራትና ቴሌ አገልግሎት በሽሬ እስካሁን  አለመጀመሩን ጠቅሰው የመልሶ ግንባታው ሥራ እንዲፋጠን ጠይቀዋል።

በተለይ የከተማው ነዋሪ የባንክና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀምሩ እየጠየቀ መሆኑንም አንስተዋል።

በከተማዋ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የተለያዩ ህዝባዊ አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ መሆኑንም አቶ ብርሃኑ አብራርተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለማ ተሰማ በበኩላቸው፣ በክልሉ የመልሶ ማቋቋም ስራ ህዝቡ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ፣ መከላከያ ሠራዊትና መንግሥት የየራሳቸው ድርሻ አላቸው ብለዋል።

በተለይም በማንኛውም ሁኔታ የጦር መሳሪያ ያላቸው፣ በጫካም ሆነ በበረሃ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ካሉ ትጥቃቸውን ለሚመለከተው አካል አስረክበው ሰላማዊ ህይወታቸውን መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

መርማሪ ቦርዱ በህዝቡና በጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚነሱ ድጋፍ፣ እገዛና መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮችን እየተከታተለ የሚመለከተው አካል እንዲፈታ በትኩረት ይሰራል ሲሉም አቶ ለማ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም