“አራዳ በሀገር ፍቅር” የፎቶ አውደ ርዕይ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለእይታ ይቀርባል

107

አዲስ አበባ ታህሳስ 10/2013 (ኢዜአ) “አራዳ በሀገር ፍቅር” የፎቶ አውደ ርዕይ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለእይታ ክፍት እንደሚሆን የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ኃላፊ ሠርፀ ፍሬስብሐት የስዕል አውደ ርዕዩ ዕይታዊ ጥበብን ለማበረታታትና ለዕይታ እንዲበቁ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

“ብዙ ጊዜ የኪነ-ጥበብ ዕይታዎች ወደ ክወናዊ ጥበባት ያደላሉ።” ያሉት ኃላፊዉ ቢሯቸው የተቋቋመበት አንዱ ዓላማ በዕይታዊ ጥበብ ላይ ትኩረት አድርጎ ለመስራት እንደሆነ ተናግረዋል።

በስዕል አውደ ርዕዩም የአዲስ አበባን ገፅታ በከፊል የሚያሳዩ ፎቶዎች ለእይታ ይቀርባሉ ብለዋል።

ለዕይታዊ ጥበብ ትልቅ እውቀት ያላቸዉ ሰዎች በሀገራችን ቢኖሩም በፎቶ ግራፍ መስክ ብዙ ተሳትፎ ስለሌለ ከባለሙያዎች ጋር በመሆን የፎቶ ግራፍ ጥበብ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ልምድ እንዲወስዱ መዘጋጀቱንም ገልፀዋል።

በአውደ ርዕዩ የሚሳተፈው ፈረንሳዊው ሰባስቲያን ካዮ፤ የፎቶ አውደ ርዕዩ በአፍሪካ ለኪነ-ጥበባዊ ድርጊት ቀዳሚ ምልክት በሆነው ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት መካሄዱ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጥ ገልጿል።

የአውደ ርዕዩ ዋና ዓላማም የአዲስ አበባ አራዳ አካባቢን መረጃ ሰብስቦ በፎቶ ለመያዝ መሆኑን ሰባስቲያን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ የኪነ-ጥበብ ሰዎችን በጋራ በማቋቋም የልምድ ልውውጥ በሚደረግብት በዚህ የፎቶ አውደ ርዕይ ኢየሩሳሌም አበራ፣ ሰሎሜ ሙለታ እና ዳንኤል ዓለማየሁ የተባሉ ኢትዮጵያዊያን ፎቶግራፈሮች እንደሚሳተፉ ታውቋል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ ከታህሣሥ 12 እስከ 15 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለእይታ ክፍት የሚደረግ ሲሆን ታዳሚዎችም በነፃ ገብተው መመልከት ይችላሉ ተብሏል።

ከታህሣሥ 13 እስከ 15  የሠዓሊዎች፣ የህፃናት እና የሕዝብ ውይይት ቀን በሚል የፎቶ አውደ ርዕዩ ሰባስቲያን ካዮ ተናግሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በቀለም መፃፍ፣ በቀለም መሳል እና የስቱዲዮ ፎቶ የማቅረብ ተግባራት እንደሚከናወኑም ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም