የኢንቨስትመንት ሕግ ማሻሻያዎቹ የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ያግዛሉ

76

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/201 (ኢዜአ) በኢንቨስትመንት ሕጉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያወጡ የውጭ ባለሃብቶችን መሳብ እንደሚያስችሉ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና የውጭ ባለሃብቶች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የኢንቨስትመንት ሕጉን በማሻሻል ለውጭ ባለሃብቶች የተመቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር እየሰራ ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የንግድ ማኅበረሰብና የውጭ ባለሃብቶችም የተሻሻለው ሕግ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት በተለይም ደግሞ ለውጭ ባለሀብቶች በሯን ክፍት እያደረገች መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኤርሚያስ እሸቱ አገሪቷ ከዚህ ቀደም ለኢንቨስትመንት የነበራት ምቹነት "ዝቅተኛና የማይስብ" ነበር ይላሉ።

የአሜሪካ 50 የሚደርሱ ባለሃብቶችን በሚወክለው  ምክር ቤት በተለይ ከውጭ ምንዛሬና ከኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይቀርቡ እንደነበር ተናግረዋል።

አሁን በአገራዊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም መነቃቃት በመፈጠሩ የኢንቨስትመንት ሕጉ መሻሻል ተስፋ ሰጪ ጅማሮ ነው ብለዋል።

ባለሃብቶች በአገሪቷ ለሚያፈሱት መዋዕለ ነዋይ መተማመን እንደሚፈጥርላቸውም ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።

አሜሪካዊው ባለሃብት ሚስተር ሂሮኪ ሳያማ ቀደም ሲል የነበረው የኢንቨስትመንት ሕግ ያስቀመጣቸው ገደቦች ለውጭ ኢንቨስተሮች ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ።

ይህን ያሉት በሁለት ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ልምዳቸው በመነሳት ነው።

ካላቸው ልምድና እይታ አኳያም በሕጉ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች ባለሃብቶችን በስፋት ማሳተፍ ያስችላል ነው ያሉት።

የኢኮኖሚ ማሻሻያወ በፍጥነት ወደ ተግባር ሲቀየር ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኢንቨስትመንት ተመራጭና ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋት ባለሀብቱ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም