የጁንታውን አባላት የማደንና ሰላምን የማስፈን ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል¬ ብርጋዴል ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ

64

አዲስ አበባ ታህሳስ 9/2013 (ኢዜአ) በአካባቢው ሰላም የማስፈንና እጅ ያልሰጡ የጁንታውን አባላት የማደን ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን በሰሜን ዕዝ የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦር አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ ተናገሩ።

የህወሃት ጁንታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በዳንሻ በሚገኘው የ5ኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ላይ የፈፀመውን ጥቃት በመመከት የህግ ማስከበሩን ከመሩት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከል ሙሉዓለም አንዱ ናቸው፡፡

የአገር መከላከያ ሰራዊት በጁንታው ላይ የወሰደውን የህግ ማስከበር ስራ አጠናቆ አሁን ላይ ወንጀለኞችን የማደንና መልሶ ግንባታ ላይ ይገኛል።

ይህንኑ አስመለክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ፤ ከህግ ማስከበሩ መጠናቀቅ በኋላ የተበታተኑ የጁንታውን አባላት የማደን ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በምዕራብ በኩል የሚገኙ አካባቢዎች ከጁንታው መወገድ በኋላ የፀጥታ ስጋት እንደሌለም ገልጸዋል።

የብርጋዴል ጀኔራል ሙሉዓለም እዝ በሚቆጣጠረው ከዳንሻ ጀምሮ ባሉ የምዕራብ አካባቢዎች የማህበረሰቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴ የማጠናከርና የማረጋጋት ስራዎች በውጤታማ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ጉዳት ይደርስብናል በሚል ፍርሃት ከአካባቢው ርቀው የነበሩ ዜጎቸም ወደየ መኖሪያ ቀያቸው ተመልሰው የግብርና ምርት በመሰብሰብ ላይ ሲሆኑ የንግድ ስራዎችም በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ አባላት ጋር በመሆን በየቀበሌው ኮሚቴ በማዋቀር አካባቢውን እየጠበቀ ሲሆን በከተሞች ሆቴሎችን ጨምሮ የንግድ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በየአካባቢው ተቆራርጠው የቀሩ የጁንታው ታጣቂዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ  በማድረግ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን በርካቶች ትጥቃቸውን እንዲያስረክቡ አድርገናል ሲሉም ብርጋዴል ጀኔራል ሙሉዓለም ገልጸዋል።

አሁንም ጥቂት የቡድኑ ጥቅመኞች በየቦታው መኖራቸውን ያነሱት ብርጋዴል ጀኔራል ሙሉዓለም እያደንን ለህግ እናቀርባቸዋለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም