የትግራይ ህዝብ አጋርነት

125

በአብዱራህማን ናስር /ኢዜአ/ 

በትግራይ ክልል በምዕራባዊ ዞን በሃፍታ ሁመራ ወረዳ በምትገኘው የማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ክስተት ተፈጠረ። የከተማው ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ሳምሪ የሚባለው ኢ-መደበኛ የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች ቡድን በአንድነት በመሆን በየጎዳናው እና ከቤት ቤት በመዘዋወር በንፁሃን ዜጎች ላይ ዘግናኝ ጥቃት ፈጸሙ። ማንም ሰው ማምለጥ እንዳይችል ሚሊሻዎች እና ፖሊሶች በየመንገዱ መታጠፊያዎች አድፍጠው በመጠበቅ እየተኮሱ ይመልሱ ነበር። 

በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንዲት የትግራይ ተወላጅ 13 ሰዎችን በቤቷ ደብቃ ህይወታቸውን ታድጋለች። አጥቂው ቡድን ተመልሶ መጥቶ እንዳያገኛቸው በመስጋትም በሌሊት ደብቃ ወደ እርሻ ቦታ በመውሰድ አብራቸው ተደብቃ ቆይታለች። በማግስቱ ሁኔታው ሲረጋጋ በህይወት ከተረፉት ጋር ወደ ከተማ መመለሳቸውን ከጉዳቱ የታደገቻቸው መናገራቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን አስመልክቶ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያመለክታል።

የህወሃት ጁንታ ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ  ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ መንግስት በጀመረው ህግ የማስከበርና የሀገር ሉአላዊነትን የማስጠበቅ ዘመቻ የትግራይ ህዝብ ከመከላከያ ጎን በመሆን አጋርነቱን አሳይቷል።

የህወሃት ጁንታ ቡድን ለ27 ዓመታት ወደ ስልጣነ መንበሩ እንዲመጣ መሠረት ለሆኑት የትግራይ ህዝብ ከስም ውጪ እምብዛም የፈየዱለት ነገር እንደሌለ የክልሉ ተወላጆች ይገልጻሉ። ተወላጆቹ ከሰሞኑ ባካሄዱት ውይይቶች እንደገለጹት የህወሃት ጁንታ ቡድን የብዙሃኑን ፍላጎትና ጥያቄ በመጨፍለቅ ለጥቂቶች የተደላደለ ህይወት አመቻችቶ በህዝቡ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ኖሯል። ቡድኑ በልማት ስም ከህዝቡ መዋጮ ሲሰበስብ እንደነበር የሚያስታውሱት ነዋሪዎቹ ህዝቡ ግን አሁንም የተጎሳቆለ ህይወት እየመራ ይገኛል ሲሉ ይገልጻሉ። የጁንታው ቡድን ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አፍኖ በመያዝ በክልሉ ተወላጆች ላይ ጫና ሲያሳድርም እንደነበር ያስታውሳሉ። የተለየ አቋም በሚያነሱት ላይ እስራት አሊያም ከሥራ የመታገድ እጣ ይደርስበታል በማለት በምሬት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የህወሃት ጁንታ ቡድን በስልጣን ላይ ቆይታው የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ኢትየጵያውያን ወገኖቹ በጋራ እንዲኖሩ ከማመቻቸት ይልቅ የሚነጣጥሉ ጉዳዮች ላይ ሲሰራ ኖሯል። ባለፉት ሁለት አስር አመታት ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ልዩነታቸው ላይ ተጠምደው የጋራ ሀገራቸው እና በብዙ ሺ አመታት የገነቡዋቸው የጋራ እሴቶቻቸውን የማጥፋት፣ የበዳይ እና ተበዳይ ፖለቲካን በስልጣን መቆያ መሳሪያነት ተጠቅሞበታል።  የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወገኖቹ ጋር አንድ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች ይልቅ የሚለያዩዋቸው ጉዳዮች ላይ ሲሰራ እንደነበርም ብዙዎች የትግራይ ተወላጆች ይናገራሉ።

በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የጁንታው ቡድን መቀሌ ከመሸገ በኋላ ህዝቡን በተለያየ ፕሮፖጋንዳ ሲደልለው ከርሟል። ይህ ቡድን የትግራይን ህዝብ ስነልቦና ለመያዝና በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው በማሰብ “የፌዴራል መንግስቱ ሊጨፈልቅህ ነው፣ አሃዳዊ ስርዓት ሊጭንብህ ነው፣ ከሻዕቢያ ጋር ሊወጋህ እየተዘጋጀ ነው” በማለት የሀሰት ትርክት ተርኳል። 

የጁንታው ቡድን በሀገራዊ ለውጡ ምክንያት ቀደም ሲል ተቆጣጥሮት የነበረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የበላይነት በማጣቱ እና ተጠያቂም እንደሚያደርገው በመገንዘቡ ለበርካታ ዓመታት ዞር ብሎ ያላየውን ህዝብ “አሁን ትግራይን በሙሉ ሀይላችን ለመካስ መጥተናል” በሚል ሽንገላ ህዝቡን ለመያዝ ሞክሯል። በወቅቱ ህዝቡ እውነት መስሎት ተቀብሏቸው የነበረ ቢሆንም፤ በሂደት ግን ለክልሉ ህዝብ ችግሮች መፍትሄ ከማፈላለግና ከመፍታት ይልቅ የማዕከላዊ መንግስት ስልጣንና የሀገር ሀብት መልሶ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸውን ወታደራዊ ዝግጅት ማድረግ መጀመራቸውን በትዝብት ተመልክቷቸዋል።

ይህ የጁንታው ቡድን የግፍ ጽዋው ሲሞላ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጦርነት ከፍተ። ሠራዊቱ ለ21 ዓመታት ያህል የትግራይን ህዝብና የሀገር ዳር ድንበርን እየጠበቀ ባለበት በጁንታው ቡድን ክህደት ተፈጽሞበታል። ሜጀር ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ (አባ መላ) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደጠቀሱት የጁንታው ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ወንጀል በምንም አግባብ ይቅርታ የሚያሰጠው አይደለም። ለ21 ዓመታት አብሯቸው በኖረ ሠራዊት ላይ የተሠራው ወንጀል በዓለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ ነው። በተመሳሳይ የጁንታው ቡድን በማይካድራ በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው ጅምላ ጭፍጨፋ እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊነት የተሞላ አጸያፊ ተግባር ነው። 

የጁንታው ቡድን ዓላማ ባለፉት 27 ዓመታት የሰራውን ጥፋት ከተጠያቂነት ለማምለጥ፣ ሀገሪቱን ደግሞ ወደ ማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ለመክተት ነበር። የጁንታው ቡድን ህዝቡን በጦርነት ለመማገድ “የትግራይ ህዝብ ሙሉ በሙሉ ከእኛ ጋር ይሰለፋል” ብለው ነበር። አመራሮቹ በየእለቱ በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ብቅ እያሉ “ጦርነት ተከፍቶብናል፤ የትግራይ ህዝብ ጦርነት ልማዱ ነው፣ ሊወጉን የመጡትን እንቀብራቸዋለን” በማለት በተደጋጋሚ ፎክረዋል።

የጁንታው ቡድን አመራር ሰጪው ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ህግ የማስከበር እርምጃ መወሰድ ሲጀመር በክልሉ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው “በትግራይ ክልል የነበረውን ጦር መሳሪያ በመጠቀም ትግራይን ለመጨፍጨፍ የነበረው ህልም ሙሉ በሙሉ ከሽፏል፡፡ ለአቋማችን መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ ነን፡፡ አሁን ከነሙሉ ወታደራዊ ትጥቃችን ተዘጋጅተናል፡፡ እነዚህን ጦር መሳሪያዎች ትግራይን እንጠብቅባቸዋለን፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚቃጣብን ወረራ እንደመስስበታለን፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ታጥቀናል” ሲሉም ተደምጠዋል። ዶ/ር ደብረጽዮን በመግለጫቸው የትግራይ ክልል ህዝብ ብቻ ሳይሆን በክልሉ የሚገኘው የሰሜን እዝ ሰራዊትም ከጎናቸው መሰለፉን ተናግረው ነበር።

እነሱ ያሰቡት ግን አልሆነም።ሀገር ወዳዱ የመከላከያ ሠራዊት እና የትግራይ ህዝብ የጁንታው ቡድን እንዳሰበው ከጎኑ ተሰልፎ ቢሆን ኖሮ ሠራዊቱ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተጎናጸፈው አኩሪ ድል ባልተገኘም ነበር። የትግራይ ክልል ህዝብ የጁንታው ቡድን ካሰበው በተቃራኒ በመቆም ድጋፉን የሰጠው ለሀገር መከላከያ ሠራዊቱ ነው። ውጊያው እየተገባደደ ባለበት ወቅት የጁንታው ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ቴሌቪዥን ወጥተው “ይህ ጦርነት ህዝባዊ ጦርነት ነው፤ አድዋ ያለ ህዝብ፣ ራያ ያለ ህዝብ፣ ተምቤን ያለ ህዝብ እያንዳንዱ የትግራይ ህዝብ ጠብመንጃ የያዘም ይሁን ያልያዘ ጦር፣ ጩቤ የያዘ ሰው በሙሉ የመጣውን ሃይል ሊመክተው ይገባል” በማለት ጥሪ አስተላልፈው ነበር። የትግራይ ህዝብ ግን የህወሃት ጁንታ ቡድን ያቀረበለትን የጦርነት ጥሪ ባለመቀበል ለፌዴራል መንግስት አጋርነቱን በግልጽ አሳይቷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከፓርላማ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የትግራይ ህዝብ ስላደረገው ጀግንነት ሲናገሩ “በግጭቱ እለት መከላከያን አትመቱም ብሎ ተቃውሞ አሰምቷል፤ በዚህ ምክንያት ባንዳ ተብሎ የተመታ አለ፤ የሠራዊቱን ህይወት ለማዳን ከፍተኛ ሙከራ ያደረጉም ሰዎች ነበሩ፣ ኢትዮጵያ ስትወጋ አብሬ አልቀመጥም ወደ ኤርትራ ከወጣው ጦር ጋር እወጣለሁ ያለም ነበር፤ ጉዳዩ የኢትዮጵያዊነትና የስግብግብ ጁንታው እንጂ የኢትዮጵያና የትግራይ አልነበረም። መከላከያ ሠራዊቱ ሽሬ ሲደርስ ‘እናንተን ምቱበት ብለው ሰጥተውናል እኛ ግን አንመታችሁም’ በማለት መሳሪያዎችን አምጥተው አስረክበዋል፤ አክሱም ላይ 40 የሚጠጉ ቁስለኞችን ደብቆ አቆይቶ አስረክቦናል” በማለት ነበር የገለጹት።   

ወንጀለኛውን የጁንታ ቡድን ወደ ህግ ለማቅረብ በተከፈተው ዘመቻ የትግራይ ህዝብ በብዙ ጭንቅ ውስጥ ያሳለፈ ቢሆንም የጁንታውን ጥሪ ባለመቀበል ዓላማቸውን አክሽፏል። የመከላከያ ሰራዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል የተቀዳጀውም በዚህ ምክንያት ነው።

የጁንታው ቡድን መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት እንዲሁም ማይካድራ ላይ ትግራዋይ ባልሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው የግፍ አገዳደል ህዝቡ እርስ በርስ እንዲጋጭና እንዲገዳደል በማሰብ ነበር። ነገር ግን የጁንታው ቡድን ስሌት ሊሳካ አልቻለም። የመከላከያ ሠራዊት ነጻ ያወጣቸው አካባቢዎችና ከተሞች ነዋሪዎች “ስለ መከላከያ ሰራዊት የተነገረን ሌላ አሁን እያየንና እየተደረገልን ያለው ሌላ ነው” ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ከመከላከያ ጋር በጋራ በመሆን የአካባቢያቸውንና የከተማቸውን ሰላም ለመመለስ ሰርተዋል።

በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታዎችን እንዲዘግቡ ወደተለያዩ የውጊያ ግንባሮች ተልከው ህዝቡንና የመከላከያ ሰራዊቱን በቅርበት ሲያነጋግሩ የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንደገለጹት የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን እንዲገድሉ ተልዕኮ የተሰጣቸው የጦሩ ምግብ አብሳይ ሴቶች ነበሩ፤ ነገር ግን እንዲህ አይነት ክህደት አንፈጽምም ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የህወሃት ጁንታ ቡድን ለህዝቡ ባሰራጨው የተሳሳተ መረጃ “መከላከያ ቢያገኛችሁ ይገድላችኋል ስለዚህ ልትዋጉት ይገባል” በሚል መሳሪያ እስከማስታጠቅ የደረሰ ቅጥፈት ሲነዛ እንደነበር ገልጸዋል።

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማይካድራ ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ አስመልክቶ የጥናት ውጤቱን ይፋ ባደረገበት ሰነድ ላይ እንደተጠቀሰው ሳምሪ የተባለው የትግራይ ተወላጅ የወጣቶች ቡድን አሰቃቂ በሆነ የጭፍጨፋ ወንጀል ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታዎች ሸሽገው በመደበቅ የብዙ ሰዎች ሕይወትን እንዳተረፉ ከጥቃቱ የዳኑ ሰዎች፣ የአይን ምስክሮች እና በወቅቱ በነፍስ አድን ተግባር ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች መናገራቸውን አመልክቷል። የትግራይ ሕዝብ ከእውነት ጋር በመቆምና የጁንታውን እኩይ ዓላማ ወደ ጎን በመተው ሠራዊቱ መቀሌ እስኪገባ ድረስ ድጋፍ አድርጓል። የጁንታው ቡድንና ህዝቡ በፍጹም አንድና ያው አለመሆናቸውንም በህግ ማስከበር ዘመቻው በገሃድ ታይቷል። መከላከያ ሰራዊቱ ህግ የማስከበር ዘመቻውን በድል አጠናቋል። ዘመቻው ህግ የማስከበር ብቻ ሳይሆን ህዝቡንም ነፃ ማውጣት ነውና የትግራይ ህዝብ ለነፃነቱ ላሳየው አጋርነት ሊመሰገን ይገባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም