አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ለሁለት ዓመት ለማሰልጠን ተስማማ

216
አዲስ አበባ ሀምሌ 13/2010 አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱና የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድንን ለሁለት ዓመት እንዲያሰለጥን ተስማሙ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብስባ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የተሾሙት አሰልጣኝ አብርሃም የሁለት ዓመት ውል የፈረሙ ሲሆን በወር 125 ሺህ ብር ይከፈላቸዋል። የማበረታቻ ሽልማትን በተመለከተ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚወስነው መሰረት እንደሚፈጸምና በቀጣይ አሰልጣኙ በእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ውል እንዲፈጽሙ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሙሉ ድምጽ ወስኗል። አሰልጣኙ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችም በውሉ መሰረት እንደሚያገኙም ተገልጿል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው የሚረከቡትን ከባድ ሃላፊነት በብቃት እንዲወጡና ብሔራዊ ቡድናችን የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የእግር ኳስ ቤተሰቦች የተለመደ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉላቸው ፌዴሬሽኑ ጥሪውን አቅርቧል። አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ የሆኑት ከጅማ አባ ጅፋር ክለብ ዋና አሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ፣ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም፣ከመከላከያ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ፣ ከቀድሞው የሃዋሳ ከተማ ክለብ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር ተወዳድረው ነው። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ታህሳስ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ከብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ከተነሱ በኋላ ላለፉት ሰባት ወራት ያለ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ቆይቷል። እ.አ.አ በ2019 በካሜሮን በሚካሄደው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከሴራሊዮን የምታደርገው ጨዋታ የአሰልጣኝ መብራቱ በብሔራዊ ቡድኑ የሚያደርጉት የመጀመሪያ የውድድር ጨዋታ ነው። አሰልጣኝ አብርሃም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብሔራዊ ቡድኑ ከገባበት የውጤት ማጣት በማውጣት ቡድኑን በአህጉር አቀፍ መድረክ ተወዳዳሪ የማድረግ ፈተና ይጠብቃቸዋል። የካፍ የአሰልጣኞች ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆነው ከመሾማቸው በፊት የየመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን የመንን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ2019 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሚካሄደው 17ኛው የእስያ ዋንጫ ማሳለፋቸው ይታወሳል። አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የቀድሞው የወንጂ ስኳር እና ጉምሩክ አሰልጣኝ ሆነው ሰርተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም