የሲቪክ ማሕበራት በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ እገዛ የሚደረግ መሆኑን የሰላም ሚንስቴር ገለጸ

99

አዲስ አበባ ታህሳስ 6/2013 (ኢዜአ) የሲቪክ ማሕበራት በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሂደት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ እገዛ የሚደረግ መሆኑን የሰላም ሚንስቴር ገለጸ።

የሲቪክ ማሕበራት በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርአ ግንባታ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ የሚጋጥሙ ተግዳሮቶች ላይ የሚመክር ውይይት ተካሒዷል።

የሰላም ሚኒስቴር የስራቴጂክ አጋርነትና የተጠሪ ተቋማት ዳይሬክተር ጀነራል ሻንቆ ደለለኝ፤ መንግስት የሲቪክ ማሕበራት ሚናቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት አላሰራ ያሉ ሕጎች እንዲቀየሩ በማድረግ አቅማቸውን የሚያጠናክሩበት መንገድ ላይም በጋራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በተለይም ችግሮቻቸውን ፈትሸው ከመንግስት፣ ከማሕበረሰቡ፣ ከተቋማትና እርስ በእርሳቸው ሊኖራቸው በሚገባ ግንኙነት ላይም አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።

ማሕበራቱ በሕዝብና በመንግሰት መካከል ሆነው በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ፣ በሰላምና ልማት ላይ ተሳትፎ በማድረግ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸዋም ጠቁመዋል።

የሕግ ባለሙያው አቶ ደበበ ኃይለሚካኤል፤ ለውይይት መነሻ ባቀረቡት ጽሑፍ በሀገሪቱ አዲሱ የሲቪክ ማሕበራት ሕግ ከፀደቀ በኋላ 2 ሺህ 500 ማሕበራት ተመዝግበው እየሰሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ይሕ ቁጥር ከሌሎች የአፍሪካ አገራት አንፃር ሲታይ በጣም አነስተኛ በመሆኑም የማሕበራቱን ቁጥርና ተሳትፎ ለማሳደግ አላሰራ ያሉ አካሔዶችን መፈተሽ  ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።

ማሕበራቱ ካሉባቸው ችግሮች መካከል መንግስትና ሕዝብን በማገናኝት ፣አንድ አገራዊ የጋራ አጀንዳ ይዞ በመንቀሳቀስና ገጽታቸውን በመገንባት ረገድ ክፍተቶች እንደሚታዩባቸውም በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

ማሕበራቱ እርስ በእርስ ተደጋግፎና ተባብሮ በመስራት ረገድ ክፍተቶች እንደሚታዩባቸው የገለጹት ባለሙያው ከወገንተኝነት በመጽዳት የውስጥ ዴሞክራሲን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል።

መንግስት የሲቪክ ማሕበራቱ አላሰራ ያሏቸውን ሕጎች  በመቀየር ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው ቢሆንም ማሕበራቱን የልማት አጋር አድርጎ በማየት ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ፕሮጃይኒስት ከተሰኝ የሲቪል ማሕበር የተሳተፉት ወይዘሮ ነፃነት መንግስቱ በበኩላቸው ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በዘርፉ አሰሪ የሆነ ሕግ መጽደቁ  ተሳትፏችንን እንድናሳድግ ረድቶናል ብለዋል።

ሕጉ በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታና ሰላም ላይ ተሳትፎ ለማድረግ በር የከፈተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ማንኛውም የሲቪክ ማሕበር ከተሰማራበት መስክ ውጭ በሀገራዊ መግባባትና ሰላም ላይ መስራቱ ቅዲሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ገልፀዋል።

ፓስቸራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ ከተሰኝው የሲቪ ማሕበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተዘራ ጌታሁን፤ የሲቪክ ማሕበራት በዋናነት በሀገሪቱ የሰላም ግንባታ ላይ ይመለከተናል ብለው መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም