አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆኑ

78
አዲስ አበባ ሐምሌ 13/2010 አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬ ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን  የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። አዲሱ ተሿሚ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን በመተካት ቡድኑን በምክትል አሰልጣኝነት ያሰለጥናሉ። አሰልጣኝ ደረጄ ከዚህ በፊት የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው አገልግለዋል። ኢትዮጵያ በመጪው ዓመት በታንዛኒያ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር የማጣሪያ ጨዋታዎች ይጠብቋታል። ከዚህም ሌላ ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በታንዛኒያ በሚካሄደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ይሳተፋል። የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ለማስተናግድ በካፍ የተመረጠችው ታንዛኒያ የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካ ክፍለ አህጉር የማጣሪያ ጨዋታዎችንም ታስተናግዳለች። የማጣሪያ ጨዋታው የሚካሄደው  የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካን ወክሎ በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ነው። በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም በቡሩንዲ በተካሄደው ከ17 ዓመት በታች የምስራቅ አፍሪካና መካከለኛው አፍሪካ ሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር ተሳትፎ የነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሶማሊያ ጋር በነበረው ጨዋታ ሶስት ተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነት ክስ ቀርቦባቸው ከውድድሩ እንዲሰናበቱና አንድ ጨዋታ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን መደረጉ ይታወሳል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም