የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

62
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ሳቢያ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ። ገንዘቡ የተሰባሰበው ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፣ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞችና ሌሎች የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አካላት መሆኑ ተገልጿል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደ ሀና ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ የተሰባሰበውን በጠቅላላ 2 ሚሊዮን 361ሺህ 750 ብር ለፌዴራል አደጋ ስጋት መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን አስረክበዋል። በአገሪቱ በተለይም በኦሮሚያና ሱማሌ ክልል በተፈጠረው አለመረጋጋት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች በመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍ ብቻውን በቂ አለመሆኑን ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ጊዜ ገልፀዋል። ይህንን በመገንዘብ የመረዳዳት ባህላችንን ለማሳደግና ሌሎች የአገሪቱ አቻ ተቋማትንም ለማነሳሳት ሲባል የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ፕሬዝዳንቱ አክለው ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና የተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ማቲዎስ አንሰሙ በበኩላቸው እንደተናገሩት የገንዘብ ድጋፉ የተገኘው የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ከምግብ ወጪያቸው ቀንሰው ሲሆን ሰራተኞቹ ደግሞ ከደሞዛቸው በማዋጣት ነው። ተማሪዎቹ ገንዘቡን ለማዋጣት የወሰኑት በኦሮሚያና በሱማሌ ክልል በዜጎች ላይ የደረሰውን መፈናቀል በማየት በራሳቸው ተነሳሽነት ጥያቄውን በማቅረባቸው መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንት ተማሪ ጃዋር ሱልጣን ተናግሯል። ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኙና ከደረሰባቸው ጉዳት እስኪያገግሙ ሌሎች የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሰራተኞችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። በፌዴራል አደጋ ስጋት መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን የአቅርቦትና ሎጂስቲክ ዳይሬክተር አቶ አይደሩስ ሀሰን ከኦሮሚያና ሱማሌ በተጨማሪ በአማራና በትግራይ ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖች ስለሚገኙ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተገኘው ድጋፍ እነርሱንም ያጠቃልላል ብለዋል። በድርቅ፣ በጎርፍና ከግጭት ጋር በተያያዙ ክስተቶች አልፎ አልፎ በአገሪቱ በዜጎች ላይ መፈናቀል ስለሚከሰት ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈችና ለማህበረሰብ ደራሽ መሆናቸውን ማሳየት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም