በጌዴኦና ጉጂ ዞኖች የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረግ ጥረት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ምሁራን ገለፁ

48
ዲላ ሀምሌ 12/2010 በጌዴኦና ጉጂ ዞኖች የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ እንዲሚያበረክቱ የጌዴኦ ዞን ምሁራን ገለፁ ፡፡ ምሁራኑ በአካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ ችግርና የመፍትሔ አቅጣጫ ዙሪያ ዛሬ በዲላ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂደዋል ፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ተስፋፅዮን ጴጥሮች በጌዴኦና ጉጂ ዞኖች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ዙሪያ በዞኑ ያሉ ምሁራን በተበታተነ መልኩ ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ መቆየተቸውን ገልፀዋል፡፡ ምሁራን ወጥነት ያለው የመፍትሄ ሀሳብ መጠቆም እንዲችሉ በማሰብ መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል ፡፡ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በርካታ ዜጎች መፈናቀላቸውን የተናገሩት መምህሩ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መቋቋምና ወደቀድሞው ሠላማዊ ሕይታቸው መመለስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ምሁራኑ ከመንግስትና ሌሎች ተቋማት ጎን በመቆም ጥናት ላይ የተመሠረተና የመደመር እሳቤን የሚያጠናክር የመፍትሄ ሀሳብ በማፍለቅ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ መምህር ተስፋፅዮን ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ በግልና በቡድን እየተንቀሳቀሱ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከተማሪዎቻቸውና ከዩኒቨረትሲቲው ማህበረሰብ ጋር ባላቸው ግንኙነት ለዘላቂ ሰላም የሚበጅ ሀሳብ በማፍለቅ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክቱ አስረድተዋል ፡፡ በተጨማሪም መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናዠውን አረጋግጠዋል፡፡ በዲላ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መምህር ተረፈ ሾንጦ በበኩላቸው ''መንግስት ለጉዳዩ እልባት ለመሰጠት ከሚያደርገው ጥረት በተጓዳኝ ምሁራን የችግሩ መንስኤ ላይ ጥናት በማካሄድ የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይጠበቅብና''ል ብለዋል፡፡ ችግሩ ተደጋጋሚ በመሆኑ ሥር ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው የገለፁት መምህር ተረፈ በጌዴኦና ጉጂ ዞኖች የሚገኙ ምሁራን ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ በተለይ በዲላና ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ምሁራን በመተባበር ሰፋ ያለ ጥናት በማካሄድ ዜጎች ዘላቂ መፍትሄ የሚያገኙበትን መንገድ ማመላከት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡ መምህር ተረፈ ''በማህበራዊ ሚዲያዎችም በጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች መካከል ፍቅርና አንድነትን የሚያጠናክሩ ተጨባጭ መልእክቶችን በማስተላለፍ ምሁራን ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል'' ብለዋል ፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅዖ እንዲሚያበረክቱም አክለው ገልፀዋል ፡፡ የጌዴኦ ዞን ምሁራን ህብረት ሰብሳቢ አቶ ክብሩ ማሞ በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት ''በዞኑ በርካታ መፍትሔ የሚሹ ችግሮች ቢኖሩም ምሁራን እስካሁን የሚጠበቅብንን ስራ አልሰራንም'' ብለዋል ፡፡ በአካባቢው የሚከሰቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመንግስት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ የሁለቱን ህዝቦች ዘላቂ ሠላምና አንድነት ለማረጋገጥ ምሁራን በስፋት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡ መድረኩን የመሩት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው የፀጥታው ችግር በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ የሚኖሩ የጌዴኦ ብሔር ተወላጆች ወደ ጌዴኦ ዞን መፈናቀልን ተከትሎ የተከሰተ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአዋሳኝ አካባቢ በነበሩ ግጭቶች ችግሩ ተባብሶ በርካታ ዜጎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል ፡፡ እስካሁንም በነዚሀ አዋሰኝ አካባበዎች ትንኮሳዎች መቆም አለመቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃይ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ በመሆኑ የዞኑ ምሁራን ሌሎች ጉዳዩችን ወደጎን በመተው ከአስተዳደሩ ጋር በመተባበር ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ የዞኑ ምሁራን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚያካሂዱት ጥናት በተጓዳኝ በሰብአዊ ድጋፍ ስርጭት፣ በህክምናና ሌሎች የሰው ሀይል በሚሹ ጉዳዮች ላይ ጉድለቶችን በመሙላት ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት ለተፈናቀሉ ዜጎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡና ዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተጠብቀው የሚኖሩበት ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው ምሁራን ባወጡት ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ ጠይቀዋል፡፡ በውይይት መድረኩ 500 የሚሆኑ የዞኑ ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን በዕለቱ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሆን ከ120 ሺህ ብር በላይ ተሰብስቧል ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም