በማንነት ጥያቄያችን ብቻ ከእስርና መንገላታት ነጻ መውጣታችን አስደስቶናል…በከሃዲው ህወሃት ታስረው የነበሩ ሰዎች

65

ማይጨው፤ ታህሳስ 4/2013(ኢዜአ) ከብዙ እንግልትና መከራ በኋላ በሃገር መከላከያ ሰራዊት እገዛ ነጸ ወጥተው በሰላም ወደ ቤት መመለሳቸው ዳግም የተወለዱ ያህል እንደተሰማቸው የራያ አላማጣ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል አቶ ብርሃኑ በላይ “በህጋዊ መንገድ የራያ ማንነት ጥያቄ በማንሳታችን የትግራይን አንድነት አፍርሳችኋል፣ ሰልፍ አስተባብራችኋል በሚል ተልካሻ ምክንያት ላለፉት ሁለት አመታት በህወሓት ማጎርያ ቤቶች እንግልት እና ስቃይ ደርሶብኛል” ብለዋል።

ከ2011 ዓ.ም በህገ ወጡ የህወሓት ቡድን እጅ ውስጥ ከገቡ ጀምሮ በእምባ አላጄ፣ እንዳመኾኒ፣ ማይጨው እና በመቀሌ ባዶ ስድስት እና ማረሚያ ቤቶች ሲንከራተቱ እንደነበርም ገልፀዋል።

“በእስር ቤት በቆየሁባቸው ጊዜያት የጸሀይ ብርሃን አላገኝም ነበር ከፍተኛ ድብደባም ተፈፅሞብኛል” ብለዋል።

በመቀሌ ማረሚያ ቤት በነበሩበት ወቅት የመከላከያ ሰራዊት ወደ መቀሌ እየተጠጋ ሲመጣ ሌሎች እስረኞች ሲፈቱ የራያ፣የወልቃይት እና የኤርትራ ሰላይ ብሎ ያሰራቸው ሰዎች ወደ ተምቤን ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውንም ተናግረዋል።

"መንግስት በህወሓት ላይ በወሰደው ህግን የማስከበር እርምጃ ሲሸነፍ የማንነት ጥያቄ ያነሳን 64 ሰዎች የሞት ፍርድ ቢፈረድብንም የአብይ አዲይ ማረሚያ ቤት ምክትል አስተዳዳሪ ኮማንደር ሐጎስ ውሳኔው እንዳይፀና በማድረጉ ባለቀ ሰአት መከላከያችን ደርሶ ህይወታችንን ታድጎናል" ብለዋል።

"አሁን በህይወት ተርፈን ከቤተሰቦቻችን መገናኘታችን ዳግም የተወለድን ያህል ስሜት ተሰምቶኛል" ብለዋል አቶ ብርሃኑ።

"የሞት ፍርድ ተፈርዶብን በመከላከያ ሰራዊት ጥረት ነፃ መውጣታችን በጣም አስደስቶኛል" ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ በራያ ማንነት ጥያቄ ምክንያት ብቻ ታስረው የቆዩት ወይዘሮ ትህንዋ አገዞም ናቸው።

"በፅንፈኛው እጅ ወድቄ በህይወት ወደ ቤት እመለሳለሁ የሚል ተስፋ አልነበረኝም፤ አሁን ግን በሰላም ተመልሼ ከቤተሰቦቼ ጋር መገናኘት ችያለሁ" ብለዋል።

እስረኞቹ ከሞት ፍርድ አውጥቶ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ላደረጋቸው የሃገር መከላከያ ሰራዊት እና ወደ አላማጣ ሲገቡም ደማቅ አቀባበል ላደረገላቸው የከተማው ነዋሪ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የማንነት ጥያቄ በማንሳታቸውና በፖለቲካ ልዩነታቸው ምክንያት በህወሓት ጁንታ ቡድን ታስረው የነበሩ 64 ሰዎች በመከላከያ ሰራዊት ጥረት ነፃ መውጣታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም