በእንዳመሆኒ ወረዳ አማራጭ የኃይል ምንጭ በመጠቀም የደን ውድመትን ማስቀረት ተችሏል

51
ማይጨው ሀምሌ 12/2010 በትግራይ ደቡባዊ ዞን የእንዳመሆኒ ወረዳ አርሶ አደሮች አማራጭ የኃይል ምንጭ መጠቀም በመቻላቸው በተፈጥሮ ደን ሃብት ላይ ሲደርስ የነበረውን ውድመት ማስቀረት እንደተቻለ ተጠቆመ። የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ እንዳስታወቀው በተጠናቀቀው የ2010 በጀት ዓመት ብቻ በዞኑ አምስት ወረዳዎች ለሚገኙ ከ42 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎችን አሰራጭቷል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አንዳንድ የወረዳው አርሶአደሮች እንዳሉት አማራጭ የኃይል ምንጭ በስፋት በመጠቀማቸው ለማገዶነትና ለከሰል ሲጠቀሙበት የነበረውን የተፈጥሮ ደን ከመቁረጥ ተቆጥበዋል። በእንዳመሆኒ ወረዳ የ "ሽፍጣ" ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አለሙ ግደይ እንዳሉት የባዮጋዝ አማራጭ ኃይል መጠቀማቸው ማገዶ እንጨት ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ ለግብርና ሥራቸው እንዲያውሉት አድርጓል። የኤሌክትሪክ ምጣድና መብራት መጠቀም ከጀመሩ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ የደን ሀብት ከመቁረጥ መቆጠባቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው አርሶአደር ግርማይ ኃለፎም ናቸው፡፡ "አማራጭ የኃይል ቴክኖሎጂ መጠቀሜ ቀደም ሲል በጭስ ምክንያት በዓይኖቼ ላይ ሲደርስ የነበረውን ጉዳት ሙሉ በሙሉ አስቀርቶልኛል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የ‘‘ሰረንጋ‘‘ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አማካለች ሰመረ ናቸው፡፡ የዞኑ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ተጠባባቂ ኃላፊ አቶ ተሾመ ደበሳይ በበኩላቸው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑ ለሚገኙ ከ42 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ታዳሽ የኃይል ማመንጫ ቴክኖሎጂዎች እንዲሰራጩ መደረጉን ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂዎችን ለመብራትና ለምግብ ማብሰያ አገልግሎት እየተጠቀመባቸው መሆኑንም ነው የገለጹት። እንደ አቶ ተሾመ ገለጻ ለቴክኖሎጂዎቹ ከ1 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን የዞኑ አርሶ አደሮችም እጅ በእጅ ክፍያ መግዛታቸውን ተናግረዋል። ለዞኑ አርሶ አደሮች ከተሰራጩት የታዳሽ ኃይል ማመንጫዎች መካከል ኃይል ቆጣቢና የምግብ ማብሰያ ምድጃዎች፣ ምጣዶችና በጸሐይ ኃይል የሚሰሩ የኤሌክትሪክ መብራቶች ይገኙበታል። አቶ ተሾመ እንዳሉት በዞኑ አማራጭ የኃይል ምንጭ የመጠቀም ልምድ  እየተስፋፋ በመምጣቱ በየዓመቱ ለማገዶ ጥቅም ሲባል ከአንድ ሺህ ቶን በላይ የተፈጥሮ የደን እንጨት ላይ ይደርስ የነበረውን ውድመት ማዳን ተችሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም