የአርባ ምንጭ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎች ገለጹ

124
አርባምንጭ ሀምሌ 12/2010 የአርባ ምንጭ ከተማን ሰላም ለማስጠበቅ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ። የዞኑ ጸጥታ አስተዳደር መምሪያ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለመፍትሔው እየሰራ መሆኑን አስታውቋል። በአርባምንጭ የነጭ ሳር ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ፍሬው በዛብህ እንዳሉት በቅርቡ ከተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በኋላ በቡድን የተደራጁ አካላት በከተማው እየተዘዋወሩ በማህበረሰቡ ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው። ጥቃቱ በዋናነት የህዝብ እንቅስቃሴ ባላቸው  ስፍራዎችና በጋራ በሚጠቀሙባቸው  ተቋማት ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ከተማዋ እንዳትረጋጋ ማድረጉን ተናግረዋል። ሰሞኑን በከተማዋ እየታየ ባለው ዝርፊያና ንጥቂያ በህብረተሰቡ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የሼቻ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ፋናዬ ፈይሳ ናቸው፡፡ የአባያ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ኃይለሚካኤል ጉላንታ በበኩላቸው ትላንት ከሰዓት በኋላና ዛሬ ደግሞ ረፋድ ላይ የተደራጁ ቡድኖች ባነሱት ሁከት የህብረተሰቡ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ተናግረዋል። መንግስት በአስቸኳይ በተደራጁ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል፤ የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም  ገልጸዋል፡፡ የጋሞ ጎፋ ዞን ፀጥታ አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ቤታ አንጁሎ ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ በሰጡት ምላሽ ህብረተሰቡ እርምጃ እንዲወሰድ እያቀረበ ያለው ጥያቄ ትክክል መሆኑን ጠቅሰው ችግሩን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም