የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ ነው

80
አዳማ ሀምሌ 12/2010 የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ከ96 በመቶ በላይ  መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡ በአዲሱ የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የተመራ ቡድን የኢንዱስትሪ ፓርኩ ያለበትን ደረጃ  ዛሬ ተመልክቷል። የፓርኩ አስተባባሪ ኢንጅነር ኤፍሬም በቀለ በዚህ ወቅት እንዳስታወቁት በ102 ሄክታር ላይ ያረፈው የአዳማ ኢንዱስትር ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአንድ ወር በኋላ ሥራ ይጀምራል፡፡ ግንባታው 125 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በሆነ ወጪ የሚካሄደው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሂደት ውስጥ  ከ5ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች  የሥራ እድል መፍጠሩን አመልክተዋል፡፡ አሁን ላይ ከ96 በመቶ በላይ የደረሰው የኢንዱስትሪ ፓርኩ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሙሉ በመሉ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር ከ20 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች  የሥራ እድል ያስገኛል፡፡ ፓርኩ 19 የተለያዩ ማሽኖችና መገጣጠሚያ ወርክሾፖች ፣የጨርቃጨርና ሌሎች የማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን የሚያካትት መሆኑን ኢንጅነር ኤፍሬም አስታውቀዋል፡፡ የአዳማ ከተማ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ስንደገለጹት "የኢንዱስትሪ ፓርኩ በአካባቢው ለሚኖሩ  ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር  ባሻገር ለሀገሪቱ  የኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይነት የበኩሉን አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል። የከተማው አስተዳደር ለፓርኩ ግንባታ መፋጠን እያደረገ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚቀጥልም አመልክተዋል። በፓርኩ የግንባታ ሂደት የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ያቆብ በሪሶ በሰጠው አስተያየት የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ውስጥ  የከበድ ተሽከርካሪ ኦፕሬተር በመሆን ተቀጥሮ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል። በሚያገኘውም ገቢ ቤተሰቡን እያስተዳደረ ተጠቃሚ መሆኑንም ጨምሮ ገልጿል፡፡ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ በ2008 መጨረሻ አካባቢ የተጀመረ ሲሆን በቀጣይም ሁለተኛና ሶስተኛ ምዕራፎች ይኖሩታል፤ሁሉም ሲጠናቀቅ እስከ 60 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ቀደም ብሎ ስራ የጀመረው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሲሆን ቦሌ ለሚ፣ መቀሌ ፣ ኮምቦልቻ፣ ድሬደዋና ሌሎችም ተመሳሳይ ፓርኮች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መገንባታቸውና በግንባታ ሂደት ላይ እንዳሉ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም