በሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ ስለተገኘው የሰው አጽም የሚያጣራ ቡድን ሥራውን ጀመረ

62
ሐረር ሀምሌ 12/2010 በሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽን ግቢ ውስጥ ስለተገኘው የሰው አጽም ጉዳይ የተቋቋመ አጣሪ ቡድን የምርመራ ሥራ መጀመሩን የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ አቶ አበበ መብራቱ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ባለፈው ማክሰኞ ሐምሌ 9 ቀን 2010 ዓ.ም የሰው አጽም በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ሊገኝ የቻለው ከወጣቶች በደረሰ ጥቆማ መሰረት ነው። በተመሳሳይ በደረሰ ሌላ ጥቆማ መሰረት በቅጥር ግቢው ባለ የመሳሪያ ግምጃ ቤት ውስጥ ተጨማሪ የሰው አጽም መገኘቱን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት የተገኘው አጽም ከወንጀል ጋር ስላለው ጉዳይ፣ እንዴት በቦታው ሊገኝና ሊቆይ ቻለ የሚሉና መሰል ጉዳዮችን ለማወቅ እራሱን የቻለ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ የማጣራት ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል ። የማጣራት ሥራ በክልሉ በተዋቀረ የምርመራ ቡድን ብቻ የሚያበቃ አለመሆኑንና ለዲ.ኤን.ኤ እና ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች ፌዴራል መንግስትና የሚመለከታቸው አካላት እንደሚገቡበት ገልጸዋል። አቶ አበበ አያይዘው እንዳሉት ፖሊስ እያደረገው ባለው ምርመራ  የሃይማኖት አባቶችና አገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ድጋፍ ያደርጋሉ። በአሁኑ ወቅትም የተገኘው አጽም በቅጥር ጊቢው በሚገኝ አንድ ክፍል ውስጥ የተጠናከረ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል። የምርመራ ውጤቱን በተመለከተም ቢሮው የደረሰበትን ሁኔታ ለህብረተሰቡ እንደሚያሳውቅ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም