የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር ስርዓትና የተቋማት አሰራር ግልጽ አለመሆን ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት ነው -ምሁራን

88
አዲስ አበባ ሀምሌ 12/2010 የውጭ ምንዛሬ ቁጥጥር ስርዓትን አለመተግበርና የተቋማት አሰራር ግልጽ አለመሆን ኢትዮጵያን ዋጋ እያስከፈላት እንደሆነ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ተናገሩ። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ቅንጅት ተቋም ወይም ግሎባል ፋይናንሺያል ኢንተግሪቲ ባሳለፍነው የፈረንጆች 2017 ዓመት ባወጣው ሪፖርት በዓለማችን በየዓመቱ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ከድሆች አፍ ይመዘበራል። ብዙ ዜጎች የገንዘብ ምዝበራው በባለስልጣናት እንደሚከናወን ቢያስቡም ከተመዘበረው ሃብት ውስጥ እስከ 65 በመቶ የሚሆነው ግን በኩባንያዎችና በተቋማት የግብር ማጭበርበር እንደሚፈጸም የተቋሙ ሪፖርት ያሳያል። የግብር ማጭበርበሩ ደግሞ ከውጭ አገራት በሚገቡና ወደ ውጭ አገራት የሚላኩ ምርቶችን ተገን በማድረግ የሚፈጸም ሲሆን በርካታ አገራት ሃብታቸው ወደ ውጭ አገራት መገበያያ ገንዘቦች እየተቀየረ በመዝረፍ ላይ መሆኑን የዚሁ ተቋም ዓመታዊ ሪፖርት ያስረዳል። ናይጀሪያ፣ግብጽና ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ የውጪ ምንዛሬ አሻጥር በመስራት የህዝብና መንግስት ሃብት በብዛት ከሚመዘበርባቸው አገራት መካከል ቀዳሚዎቹ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ድርጊቱ በስፋት እየጨመረ ከመጣባቸው አገራት መካከል አንዷ ሆና ተጠቅሳለች። ኢትዮጵያም በዚህ ችግር ሳቢያ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ኢኮኖሚው ትልቅ ፈተና የገጠመው ሲሆን ከችግሩ ለመውጣት በሙሰኞች ላይ እርምጃዎችን ከመውሰድ አንስቶ የተለያዩ ማሻሻያ ስራዎችን እያካሄደች ነው። ኢዜአ በነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ እና ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ዙሪያ ከምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ጋር ቆይታ አድርጓል። መንግስት የተከሰተውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመፍታትና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የዶላር ዋጋ ማሻሻያዎች ቢደረግ ተጠቃሚ እንደሚሆን ምሁራኑ ተናግረዋል። በአገሪቱ በርካታ ዶላሮች በጥቂት ግለሰቦችና ባለሃብቶች እንዲሁም በቡድኖች እጅ እንዳለ የተለያዩ ምልክቶች እንዳሉ ተናግረዋል። የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ተሾመ አዱኛ እንዳሉት የውጭ ምንዛሬ በጥቂት አካላት ላይ መከማቸቱ ኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው። በተለይ ይህን ለማስተካካል እየተተገበሩ ያሉ አሰራሮች የግልጽነት ማነስና ቁርጠኛ አለመሆን  በግለሰቦች እጅ በርካታ ዶላሮች እንዲኖሩ ከማድረጉም ባለፈ ለጥቁር ገበያ መስፋፋት በር መክፈቱን ገልጸዋል። በተጨማሪ መንግስት በወጪ ንግድ ላይ የሚያደርጋቸውን ማበረታቻዎች ተጠቅመው በብዙ ዶላር ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ማሽኖች ለተባለላቸው አላማ ስለማይውሉና የወጣውን ዶላር አትርፈው ገቢ ስለማያስገኙ አገሪቷን ለኪሳራ ዳርገዋታል ብለዋል። በባንኮች የውጭ ምንዛሬ አሰራር የተቀላጠፈ ባለመሆኑ በርካቶች ከጥቅሙ ባለፈ ጊዜን ለመቆጠብም ጥቁር ገበያን ተመራጭ ያደርጋሉ ብለዋል። መንግስትም ይህንን ፈትሾ ከባንክ ውጪ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸውና የውጭ ምንዛሬ ግብይት የሚካሄድባቸው አደረጃጀቶችን መፍጠር እንዳለበት ጠቁመዋል። ሰዎች በብዛት ወደ ህገ-ወጥ መንገድ የሚሄዱት ስርዓቱ  ሲስተሙ ኢ-ፍትሃዊ ሲሆን በመሆኑ መንግስት እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባዋል ብለዋል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየታቸውን ያጋሩን ሌላኛው የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ካሳ ተሻገር በበኩላቸው መግስት አሁን ያለውን የዶላር ዋጋ ቢቀንስ ተጠቃሚ እንደሚሆንና ኢንቨሰትመንትን ለመሳብ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። መንግስት ከዚህ በተጨማሪም የማቀነባሪያ ኢንዱስትሪ ተቋማቱን ማጠናከር፣ የአገሪቱን ሰላም ማስቀጠልና የቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር አለበት ብለዋል። የሚደረጉ የዋጋ ማሻሻያዎች በዘመናዊና ስርዓት ባለው መንገድ ካልተመራ ለመንግስት ጉዳቱ ከፍተኛ ነው ብለዋል። በቀጣይ መንግስት የተጀመረውን የአገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ህዝቡ ህገ-ወጥነትን እንዲከላከል ማድረግ፣ ዲያስፖራውና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የጡረታ ተጠቃሚዎ በአገር ውስጥ አካውንት እንዲኖራቸው ማነሳሳት ዋናኛ የመንግስት ተግባር መሆን አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም