የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 22ኛ ቅርንጫፉን በቡሌ ሆራ ከተማ ከፈተ

103
ዲላ ግንቦት 6/2010 የኢትዮጵያ ምርት ገበያ 22ኛ ቅርንጫፉን በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ ከፈተ፡፡ ስራውን ትናንት በይፋ ሲጀምር የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ እንደገለጹት ምርት ገበያው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉት ቅርንጫፎቹ ቡናን ጨምሮ ሰሊጥ፣ ነጭና ቀይ ቦሎቄ እንዲሁም ማሾ ሲያገበያይ ቆይቷል፡፡ በጉጂና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች ያለውን የቡና ምርት ለማገበያየት ታስቦ በቡሌ ሆራ 22ኛ ቅርንጫፉን ከፍቶ ሥራ እንዲጀምር ማድረጉን ተናግረዋል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲመሰረት አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ገበያ ማዕከላት በማቅረብ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝና የመደራደር አቅሙን እንዲጨምር ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ምርት ገበያው ገዥዎች ጥራቱን የጠበቀ ምርት እንዲገዙ አርሶ አደሮችና አቅራቢዎችም ግብይቱ በተፈፀመ ማግስት ገንዘባቸው ወደ ባንክ ሒሳባቸው የሚገባበትን የግብይት ሥርዐት በመዘርጋት ላለፉት 10 ዓመታት ያለምንም መስተጓጎል ስራውን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡ " የምዕራብ ጉጂ አመራርና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቡሌ ሆራ ቅርንጫፉ እንዲከፈት ጥያቄ ሲያቀርቡ ቆይተዋል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ፣ ተገቢ ጥናትና ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ቅርንጫፉ መከፈቱን አመልክተዋል። የቅርንጫፉ መከፈት የአካባቢው ምርት አቅራቢዎች ምርታቸውን ወደ ሌላ ቅርንጫፍ ለመውሰድ የሚጠበቅባቸውን ተጨማሪ ወጪና ጉዞ ከማቅለል ባሻገር በአካባቢው ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚፈጥር ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው የሚመረተው ቡና በአዲሱ የቡና ውል "ጉጂ ቡና" በሚል የጣዕም ስያሜ እንዲገለጽና ግብይቱም በዚህ መሰረት እንዲፈፀም መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው አካባቢው ከቡና በተጨማሪ በከብት ርቢ ፣ በሰብልና በማዕድን ምርት የሚታወቅ መሆኑን ተናግረዋል። በአካባቢው የሚስተዋለው ህገ-ወጥ የንግድ ዝውውርና ኮንትሮባንድ ሕብረተሰቡ ከምርቱ በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ እንዳይሆን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ህጋዊ የግብይት ሥርዐት በማስፈን አርሶ አደሩና አቅራቢው የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡ ከክልሉ የቡና ምርት 26 በመቶውን የሚሸፈነው የጉጂ ቡና እንደሆነ የገለጹት የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ በበኩላቸው በዓመት ከ58 ሺህ ቶን በላይ የጉጂ ቡና ለገበያ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡ "ጉጂ ቡና" የሚል የጣዕም ስያሜ እንዲያገኝ መደረጉም በአርሶ አደሩና አቅራቢው ዘንድ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ነው የገለፁት፡፡ በቡሌ ሆራ ወረዳ ቡና አቅራቢ የሆኑት አቶ ጎሎልቻ ጎበና በበኩላቸው በሥራው ላይ ለ20 ዓመታት መቆየታቸውን ተናግረዋል። " ከዚህ በፊት ቡናችንን ወደ አዲስ አበባ እንዲሁም ወደ ሌሎች ቅርንጫፎች ስንልክ ከሚገጥመን ከፍተኛ የመኪና ኪራይ ወጪ በተጨማሪ ወረፋ ስለሚበዛ ብዙ እንጉላላ ነበር " ብለዋል፡፡ መንግስት የዓመታት ጥያቄያቸውን ስለመለሰላቸው መደሰታቸውንም ገልፀዋል፡፡ የቡሌ ሆራ የግብይት ማዕከል ከትናንት በስቲያ ተመርቆ ሥራውን በይፋ ሲጀምር የፌዴራል፣ የክልል ከፍተኛ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት፣ ቡና አቅራቢዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም