ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የስድስት አፍሪካ አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ተቀበሉ

72
አዲስ አበባ ሃምሌ 12/2010 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አዲስ የተሾሙ የስድስት አፍሪካ አገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ በመቀበል በብሄራዊ ቤተመንግስት አነጋግረዋቸዋል። ፕሬዚዳንቱ በዛሬው ዕለት የሹመት ደብዳቤያቸውን የተቀበሏቸው አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች የሌሴቶ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ የጋቦን፣ የቻድ፣የጊኒ እና የሞዛንቢክ አምባሳደሮች ናቸው። አገራቸውን በመወከል ወደ ኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የመጡት ፕሮፌሰር ማፋ ሰጃናሚን የሌሴቶ፣ አምባሳደር ጂ ን ሊዮን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አምባሳደር ሄርማን ኢሙሞንጉላት የጋቦን፣ አምባሳደር ፋድል ሰይድ አሊ የቻድ፣ አምባሳደር ጋሱ ቱሬ የጊኒ እንዲሁም አምባሳደር አልበርቲና ማሪያ የሞዛምቢክ አምባሳደር በመሆን ነው የሹመት ደብዳቤያቸውን ያስገቡት። ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኢትዮጵያ አዲስ ከተሾሙት አምባሳደሮች ጋር ውጤታማ የሆነ ውይይት ማካሄዳቸውንም ውይይቱን የተከታተሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ገልፀዋል። አቶ መለስ ፕሬዚዳንቱ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ከአምባሳደሮቹ ጋር ውይይት እንዳካሄዱ በመግለጽ፤ በተለይም በግብርና፣ በንግድና በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ትስስር ማሳደግ እንደሚገባ መግለፃቸውን አብራርተዋል። በተለይም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ልዩ ትኩረት በመስጠት እንደምትስራ አጽንኦት የሰጡት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ፤ መንግስት ለአምባሳደሮቹ ስራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት መግለጻቸውንም ተናግረዋል። አቶ መለስ አያይዘውም ተሿሚ አዳዲስ አምባሳደሮቹ በበኩላቸው በቅርቡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያለሶስተኛ ወገን ችግሮቻቸውን በጋራ ፈትተው እርቅ በማውረድ ወደ ሰላም መምጣታቸው ለአፍሪካዊያን ትልቅ ተምሳሌት መሆናቸውን ያሳያል ማለታቸውን ገልፀዋል። በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደው እርቀ ሰላም ለፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በተምሰሌትነት የሚጠቀስ እና አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሄዱበትን ርቀት አመላካች ክስተት መሆኑን  አምባሳደሮቹ መግለፃቸውን አቶ መለስ ተናግረዋል። አምባሳደሮቹ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አስረድተዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም