ዳያስፖራው አዲስ በተከፈተው ˝የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ˝ ሒሳብ ቁጥር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ተጠየቀ

50
አዲስ አበባ  ሀምሌ 12/2010 ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተጀመረውን ስኬታማ የለውጥ ጉዞ እንዲደግፉ በተከፈተው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ሒሳብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጠየቀ። ጽህፈት ቤቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመሆን አዲስ የተከፈተውን የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ሒሳብ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እንደገለጹት በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገሪቷ የተጀመረውን ስኬታማ የለውጥ ጉዞ በገንዘባቸውና በእውቀታቸው ለመደገፍ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም ዳያስፖራው በየቀኑ ከሚጠቀመው ማኪያቶ፣ ሻይና ቡና በጀታቸው ላይ በቀን አንድ ዶላር እንዲያበረክቱ ለማስቻል 'የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አካውንት' በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከፍቷል። ስለሆነም ይህንን ሒሳብ ቁጥር ተጠቅመው ዶላሩን በማስገባት ለውጡን ለመደገፍና የተሻለች አገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ለማገዝ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። መንግስት በዚህ ረገድ የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለታለመለት የልማት ሥራ ለማዋል የሚያስችል አደረጃጀት ፈጥሮ  አደረጃጀቱንም ይፋ ያደርጋል ሲሉ አቶ አህመድ አብራርተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ባጫ ግና እንደተናገሩት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ዳያስፖራዎች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ 'የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አካውንት' ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል። ፈንዱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማቀናጀትና የልገሳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚያስችል ሲሆን የሂሳብ ቁጥሩም 1000255726725 ነው ብለዋል። ወደ ሒሳብ ቁጥሩ የሚገባውን ገንዘብ ለማስተዳደርም በባንኩ የዓለም አቀፍ አገልግሎት ልዩ ቅርንጫፍ ዴስክ ተቋቁሞ ከሂሳቡ ጋር በተያያዘ ሊኖሩ የሚችሉ ማናቸውም ጉዳይ የመከታተልና ሪፖርት የማድረግ ተግባር ያከናውናል ብለዋል። ዳያስፖራው ገንዘቡን የሚያስገባበት ሂደት ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆንም ባንኩ ከ762 በላይ ዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር ባለው የ'ስውፊት' ግንኙነትና ከ20 በላይ ከሚሆኑ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር በመስራት ላይ ነው። ይህም ገንዘቡን በቅርቡ ይፋ በሚሆን ዌብሳይት አማካኝነት ዳያስፖራው ከአካውንቱ ቀንሶ ማስገባት እንደሚችልና የባንኩን የስውፊት  አድራሻ በመጠቀም እንዲሁም ከባንኩ ጋር ከሚሰሩ የተለያዩ የሃዋላ ድርጅቶች አማካኝነት ተግባራዊ ያደርጋሉ ሲሉ አስታውቀዋል። እስካሁን በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሂሳብ ቁጥሩን በመጠቀም ገንዘብ ገቢ እያደረጉ መሆኑን  የጠቀሰው ፕሬዝዳንቱ፤ ከኢትዮጵያ የብር ኖት በስተቀር ወደ አካውንቱ የየትኛውም የውጭ አገር የብር ኖት ማስገባት ይቻላል ተብሏል። በቀጣይም ባንኩ ቀልጣፋና ፈጣን የማስተላለፊያ ዘዴዎችን ለማስተዋወቅ እየሰራ እንደሆነ ተናግረው፤ ዝርዝር ሁኔታዎች እስከሚገለጹ ድረስ በተከፈተው የባንክ አካውንቱ የጀመሩትን የማስገባት ሥራ እንዲቀጥሉበት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም