በማእከላዊ ጎንደር ዞን የተከሰተውን ተምች ለመከላከል እየተሰራ ነው

67
ጎንደር ሀምሌ 12/2010 በማእከላዊ ጎንደር ዞን ስድስት በቆሎ አምራች ወረዳዎች የተከሰተውን የአሜሪካ መጤ ተምች በባህላዊ መንገድና በኬሚካል የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡ አርሶአደሮች በበኩላቸው በባህላዊ መንገድ ተምቹን በእጅ በመልቀም የሚደረገው የመከላከል ስራ አድካሚ ቢሆንም ውጤታማ በመሆኑ እየተገበሩት እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የመምሪያው ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደተናገሩት መጤ ተምቹ የተከሰተው በዞኑ በቆሎ አብቃይ በሆኑት አለፋ፣ ጣቁሳ፣ ጎንደር ዙሪያ፣ ምስራቅና ምእራብ ደንቢያ ወረዳዎች ነው፡፡ በወረዳዎቹ በሀምሌ ወር መግቢያ የተከሰተው የአሜሪካ መጤ ተምች እስካሁን በ500 ሄክታር የበቆሎ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ሃላፊው ተናግረዋል፡፡ አርሶአደሩ በባህላዊ መንገድ በእጅ በመልቀም ተምቹን ለማስወገድ ባደረገው ርብርብ በተምቹ ተወሮ የነበረ 90 ሄክታር የበቆሎ ማሳን መከላከል ተችሏል፡፡ በተጨማሪም “በ400 ሄክታር የበቆሎ ማሳ ላይ የኬሚካል ርጭት ስራ እየተከናወነ ነው'' ያሉት ሃላፊው 100 ሊትር ፈሳሽ ኬሚካልም ለወረዳዎቹ መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡ “ተባዩ ሰፊ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን አርሶአደሩ ተገንዝቦ ማሳውን በየእለቱ እየቃኘ የተቀናጀ የተባይ መከላከል ተግባራትን ማከናወን እንዲችልም የልማት ቡድን አደረጃጀቶችን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ ነው'' ብለዋል፡፡ የአለፋ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ የኑስ ወርቁ በበኩላቸው ተምቹ በወረዳው በቆሎ አብቃይ በሆኑ ሰባት ቀበሌዎች በ300 ሄክታር ላይ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ በወረዳው በዘንድሮ የክረምት የሰብል ልማት ከ11ሺ በላይ አርሶአደሮች በ6 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ የበቆሎ ሰብል ልማት በማካሄድ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የአሜሪካ መጤ ተምችን ከዚህ በፊት በኬሚካል ርጭት ለመቆጣጠር ጥረት ቢደርግም ውጤት ያገኘሁት በእጅ በመልቀም ነው ያሉት ደግሞ የአለፋ ወረዳ ነዋሪ አርሶአደር ስጦታው ከልካይ ናቸው፡፡ ተምቹ በባህሪው በበቆሎ የሙሽራ ቅጠል ውስጥ ገብቶ እራሱን የሚደብቅ በመሆኑ ከኬሚካል ይልቅ በእጅ በመልቀም ማስወገዱ አድካሚ ቢሆንም ውጤታማና ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ቻሌ ይማም በበኩላቸው በዘንድሮ ክረምት በግማሽ ሄክታር የእርሻ መሬቴ ላይ የዘራሁት የበቆሎ ቡቃይ የሚያምር ቢሆንም በወረዳው የተከሰተው ተምቹ ስጋት ላይ ጥሎኛል ብለዋል፡፡ ስጋቱን ለመቀነስም በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ተምቹን በእጅ ከመልቀም ጀምሮ በኬሚካል ጭምር ለማስወገድ ከሌሎች አጎራባች አርሶአደሮች ጋር ቅንጅት በመፍጠር የመከላከሉን ስራ አጠናክረን እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም