ኢትዮጵያዊያን በብዝሃነት ውስጥ ያላቸውን አንድነት ሊኮሩበት ይገባል -- የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት

121

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በብዝሃነት ውስጥ ያላቸው አንድነት የሚያስደንቅና ሊኮሩበትም እንደሚገባ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ያደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት ገለጹ።

የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱ "ኑ ኢትዮጵያን በአንድ መድረክ እንያት" በሚል መሪ ሀሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያዘጋጀውን የባህል ዐውደ ርዕይ ዛሬ ጎብኝተዋል።

ምክር ቤቱ 15ኛውን የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልክቶ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ያዘጋጀው የብሔር ብሔረሰቦችን አለባበስ፣ አመጋገብና የባህል ጭፈራዎች እንዲሁም ታሪካዊ ቅርሶች የሚያሳዩ ሥዕላዊ መግለጫዎች ቀርበዋል።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያዊያን በብዝሃነት ውስጥ ባላቸው አንድነትና መተሳሰር መደነቃቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን የተለያየ አይነት አለባበስ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ትውፊት ቢኖራቸውም አንድነታቸውን ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነታቸውን እንደሚያስቀድሙ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

የትኛውም ኢትዮጵያዊ ከተለያየ ቦታ መጣሁ ቢልም አንተ ማነህ? ብለህ ስትጠይቀው "እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ'' እንደሚል የገለጹት አስተያየት ሰጪዎች፤ “ይህም አገር ወዳድነቱን ያሳያል” ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያላት ብዝሃነት ሌሎችን የሚስብና የማንነቷ መገለጫ እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን ባላቸው ብዝሃነት ሊኮሩበት እንደሚገባና ይህም ኢትዮጵያዊነትን ባስከበረ መንገድ መቀጠል እንዳለበት ነው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላቱ የተናገሩት።

በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽንና በአፍሪካ ኅብረት የዓረብ ሊግ አገራት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሳሌህ ሳህቡን “የዚህ ማህበረሰብ ብዝሃነት በጣም የሚያምር ነው” ብለዋል።

“ማንንም ብትጠይቅ እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ ይልሃል” ያሉት አምባሳደር ሳሌህ፤ ወንድሞቼና እህቶቼ የሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዚሁ እንዲቀጥሉ ነው” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የቱኒዚያ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሚስተር ዋሂድ ቤን የኑስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ያለው ብዝሃነት፣ ባሕልና ቅርስ በጣም እንደሚያስገርም ገልጸዋል።

“እውነትም ኢትዮጵያ የዓለም እናት የሰው ዘር መገኛ ናት” ብለው፤ ብዝሃነትና እንግዳ ተቀባይነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መገለጫ መሆኑን እንደታዘቡ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር ሾዛብ አባስ እና በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ የሚሲዮን ኃላፊ ሚስተር ሳማድ አሊ ላኪዛዴህም ሃሳባቸውን በመጋራት የኢትዮጵያውያንን አገር ወዳድነት፣ ብዝሃነትና ባህል የሚደነቅ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ጉብኝት ኢትዮጵያ የባሕል ሀብታም መሆኗን ለማሳየት ከመርዳቱም በላይ ለአገር ገጽታ ግንባታና ለሁለትዮሽ ግንኙነት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ እፀገነት መንግሥቱም “በኢትዮጵያ ብዝሃነት የስጋት ምንጭ ሳይሆን የፍቅር፣ የአንድነትና የኩራት ምንጭ መሆኑን መገንዘብ ይገባል” ብለዋል።

የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን "እኩልነትና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና!" በሚል መሪ ሃሳብ በመጪው ማክሰኞ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም