የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ለዘላቂ ሠላም መስፈን ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናገሩ

66

አዲስ አበባ ህዳር 26/2013 (ኢዜአ) የአከሱም ከተማ ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ዘላቂ ሠላም ለማስፈን ከመንግስት ጎን በመቆም የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚሰሩ ገለፁ።

በየዓመቱ ኅዳር 21 ቀን በከተማዋ የሚከበረው የአክሱም ፅዮን በዓል ከቀናት በፊት በአካባቢው ነዋሪዎች በሠላም ተከብሮ አልፏል።

በዓሉ ከዚህ ቀደም በርካታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ከመላው የአገሪቷ አካባቢዎች እንዲሁም ከውጭ አገራት አማኞችና ጎብኚዎች በተገኙበት ነበር የሚከበረው።

ይሁንና ዘንድሮ የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ በነበረው የሕግ ማስከበር ተግባር ሳቢያ የአክሱም ፅዮን በዓል በአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ተከብሮ አልፏል።

የአክሱም ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በዓሉን በፀሎትና በምህላ በሠላም ማክበራቸውን ተናግረዋል።

አሁን በመንግስት የተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተጠናቆ ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ የተጀመረ ሲሆን የአክሱም ከተማም ሠላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች።

የከተማዋ ነዋሪዎች የሆኑት ሃጎስ ገብረማርያም፣ ሰሎሞን ተክላይ፣ መልዓከ ምህረት ተክላይ ገብረዓብና ሊቀ ትጉሃን አብይ ገብረእግዚአብሄር ስለ በዓሉ አከባበርና አሁን ስላለው ሁኔታ እንዲህ ገልፀዋል።

ነዋሪዎቹ ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴያቸው እየተመለሱ መሆኑን በመግለፅ የሕዝቡ ፍላጎት ሠላም በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም ለዘላቂ ሠላም መስፈን እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።

ነዋሪዎቹ ለሠላማቸው መከበር ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም