በዞኖቹ ከ370 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል ተሰበሰበ

102

ደሴ/ነቀምቴ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ)- በደቡብ ወሎና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ከ370 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የዞኖቹ አስተዳደሮች አስታወቁ።

በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት በ2012/13 ምርት ዘመን መኽር ወቅት 438 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል።

በምርት ወቅቱ ከለማው አጠቃላይ መሬት ውስጥ በ230 ሺህ ሄክታር ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

ከተሰበሰቡት ሰብሎች መካከል በቆሎ፣ ማሽላ፣ ስንዴና ገብስ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

በዞኑ በአንበጣ ክስተት በሰብል ላይ ጉዳት ደርሶ እንደነበር የገለጹት ቡድን መሪው አሁን ላይ አምፎ አለፎ እየጣለ ባለው ያለተጠበቀ ዝናብ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደረስ የሰብል ስብሰባው በዘመቻ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

አርሶ አደሩ የቤተሰቡን ጉልበት በማስተባበርና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ የሰብል ስብሰባው እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በምስራቅ አማራ ሜትሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የትንበያና ትንተና ባለሙያ አቶ ዋጋዬ ባህሩ 

ባለፉት አስር ቀናት በአካባቢው መጠነኛ ዝናብ እንደነበር አስታውሰዋል ።

በሚቀጥሉት አስር ቀናትም በአካባቢው መጠነኛ ዝናብ ስለሚኖር አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ የደረሱ ሰብሎችን እንዲሰበስብ አሳሰበዋል ።

በተለይ ቆላማ አካባቢዎች የተዘራ ሰብል የሚደርስ በመሆኑ ፈጥኖ በመሰብሰብ የምርት ብክነትንና ብልሽትን መከላከል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን በ2012/13 ምርት ዘመን መኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 438 ሺህ ሄክታር መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን 140 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የነበረ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ቶለሣ ጀቤሣ እንደገለጹት በዞኑ በ2012/2013 ምርት ዘመን መኽር ወቅት 317ሺህ 268 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል።

እስከ አሁን ከ140 ሺህ ሄክታር ማሳ ላይ የደረሰ ሰብል መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

ቦሎቄ፣ ሩዝ፣ አተር፣ ባቄላ፣ገብስና ጤፍ ሰብሎች በአብዛኛው መሰብሰባቸውን አመልክተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በደቦ፣ በልማት ቡድንና፣ በቤተሰብ ደረጃ የሰብል ስብሰባውን አጠናክሮ መቀጠሉን አመላክተዋል ።

በዞኑ በ2012/13 ምርት ዘመን መኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው 317ሺህ 268 ሄክታር መሬት 10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተመላክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም