ህወሓት በፈጸማቸው ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ፍትህ ተቋማት ሊጠየቅ እንደሚገባ በዲላ ዩኒቨርስቲ የህግ ምሁራን ተናገሩ

96

ዲላ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) የህወሓት ጁንታ የፈጸማቸው ወንጀሎች ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የጣሰ በመሆኑ በዓለም አቀፍ የፍትህ ተቋማት ጭምር ሊጠየቅ እንደሚገባ በዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የህግ ምሁራን ተናገሩ።

በዩኒቨርሲቲው የህግና አስተዳደር ጥናት ኮሌጅ መምህር ሳሙኤል ታዬ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተፈጠሩ ግጭቶች ህወሃት ላለፉት ዓመታት ሲሰራ የቆየው የጥላቻና የመገፋፋት ውጤት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለህዝብ ተወካዮች ያቀረቡት ማብራሪያ የህወሃት ሴራ ከማጋለጡ ባለፈ በተደጋጋሚ ሲነሱ  ለነበሩ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

የህወሃት ቡድን ከለውጡ ማግስትም ሆነ በፊት የፈጸማቸው ወንጀሎች ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን  ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የጣሰ በመሆኑ መንግስት ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍትህ ተቋማት ጭምር ሊያቀርበው እንደሚገባ ተናግረዋል ።

ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ አመቺ የአስተዳደር ሥርዓት ነው፤ ይሁንና ባለፉት ዓመታት ሥርዓቱን ተገን በማድረግ የተሰሩ ጥፋቶችን ማከም ይገባል ብለዋል።

በማንነታቸው ብቻ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች ከማቋቋም ባለፈ በሀገራቸው የትም ቦታ ተዘዋውረው የመስራት መብታቸውን በተግባር ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዜጎችን ሰብዓዊ መብት መጣስና የሀገርን ጥቅም አሳልፎ መስጠትን ጨምሮ ህወሃት የፈጸማቸው የተለያዩ ወንጀሎች በሁሉም መመዘኛ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ የሚያስችል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአለም አቀፍ ህግ መምህር አማኑኤል ታደሰ ናቸው።

ጁንታው ህወሃት የፈፀማቸውን ወንጀሎች አጣርቶ ከፖለቲካ ፓርቲነት ከመሰረዝ አንስቶ በአህጉራዊም ሆነ አለም አቀፍ የፍትህ ተቋማት ተጠያቂ ማድረግ  እንደሚገባ አመልክተዋል።

የቡድኑ አባላት ለህግ ከማቅረብ ባለፈ ባለፉት 30 ዓመታት በህዝቦች መካከል የዘራውን ጥላቻና መጠፋፋትን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ለማስተካከል ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ምክትል ዲንና የሰብአዊ መብት ጉዳይ ተመራማሪ  አቶ እዮብ አጎቾ በበኩላቸው ካለፈው በመማር የፍትህና የደህንነት ተቋማትን ከፖለቲካ ተፅዕኖ ውጭ እንዲሆኑ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የህወሃት ቡድን በህግ ፊት ቀርቦ የእጁን እንዲያገኝ ከሀገር ውሰጥ ባለፈ የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፍ ፍትህ ተቋማት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም