በወልቃይትና አካባቢው የህወሃት የጥፋት ቡድን የፈጸመው በደል ትውልዱ ላይ ጠባሳ የሚጥል ነው - የወልቃይት ጠገዴ ነዋሪዎች

101

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) የህወሃት የጥፋት ቡድን በወልቃይትና አካባቢው የፈጸመው በደል በትውልድ ላይ ጠባሳ የሚጥል መሆኑን የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ኢዜአ ከተዘዋወረባቸው የወልቃይት አካባቢዎች መካከል ከተማ ንጉስ፣ አዲ ረመፅና ቃፍታ ከተማ ነዋሪዎች በህወሓት የተፈጸመውን በደል በመሪር ሀዘን ውስጥ ሆነው ይገልጻሉ።

የቃፍታ ሁመራ ነዋሪው የ91 ዓመቱ የዕድሜ ባለጸጋ አቶ አብዱልሃሚድ ነጋሽ በከተማዋ የመገናኛ ብዙሃን አባላት መኖራቸውን ሲያውቁ 'ከእኔ በላይ ስለተፈፀመው ግፍ የሚያወራ የለም' ነው ያሉት።

የአገር ሽማግሌው አቶ አብዱልሃሚድ የችግሩ መነሻ በ1972 ዓ.ም ገደማ ህወሓት በትጥቅ ትግል ላይ እያለ መጀመሩን ያስታውሳሉ።

እንደ አቶ አብዱልሃሚድ ገለጻ ላለፉት 40 ዓመታት የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ በህወሓት የጥፋት ቡድን ስፍር ቁጥር የሌለው በደል ተፈጽሞበታል።

"እኛ እንዳንናገር በአፋችን፣ እንዳናይ በዓይናችን፣ እንዳንሔድ በእግራችን ተደርገን በስቃይ ውስጥ ኖረናል" ብለዋል አዛውንቱ።

የከተማ ንጉስ ነዋሪዋ ወይዘሮ አዲሴ ቀለብ የህወሓት የጥፋት ቡድኑ ወንድማቸውን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ 18 ዓመት ያልሞላ ልጃቸውን ደግሞ ለውትድርና ማሰለፉን ይመሰክራሉ።

በዚህም ሳይበቃው ልጅሽን ከልዩ ኃይል ልታስወጪ ነው በማለት ለእንግልትና ለእስር ዳርጓቸው እንደነበርም ይናገራሉ።

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ ወጣት አበበ ተስፋዬ ከለውጡ በፊት 'የፖሊስ አባል አመናጭቀሃል፤ አማርኛ ዘፈን ከፍተሃል' ተብሎ 11 ዓመት ተፈርዶበት እንደነበረ ያስታውሳል።

በለውጡ በመላ አገሪቷ ታራሚዎች በይቅርታ ሲፈቱ እሱም ከአራት ዓመት እስር በኋላ ነጻ መውጣቱን ይገልጻል።

የአዲ ረመፅ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ራሔል ማለደ ላለፉት አምስት ዓመታት በተደጋጋሚ ለእስር ስትዳረግ መቆየቷን፤ ከለውጡ ወዲህም በትግራይ ምርጫ አይካሄድ ብለሻል በሚል ለእስር መዳረጓን ትገልጻለች።

የወልቃይት ጠገዴ አካባቢዎች ከህወሓት የጥፋት ቡድን ቀደም ብለው ነጻ በመሆናቸው ወደ ሠላማዊ እንቅስቃሴ እየተመለሱ መሆናቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም