ኦነግ ሸኔ በንጹሃን ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት አንታገስም--- በቦረና ዞን የተልተሌ ወረዳ ነዋሪዎች

89

ነገሌ፤ ህዳር 25 /2013( ኢዜአ ) የጁንታው ህወሓት ተላላኪ ኦነግ ሸኔ ሀገር ለማፍረስ በንጹሀን ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እንደማይታገሱ በቦረና ዞን የተልተሌ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የህግ የበላይነት እንዲከበር ኦነግ ሸኔን ለማጋለጥ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት፡፡

የተልተሌ ከተማ ወረዳ የሆኑት የሀገር ሽማግሌ አቶ አብዱባ ኑራ እንዳሉት በኦሮሞ ህዝብ ስም የንጹሀንን ደም እያፈሰሰ ላለው ኦነግ ሸኔ በተለያዩ ጊዜያት የሰላም ጥሪ ቀርቧል፡፡ 


ሆኖም ጥሪውን ውድቅ አድርጎ በኦሮሞ ህዝብ ስም እየማለና እየተገዘተ ንጹሀንን መግደል፣ ሴቶችን መድፈርና አፍኖ መውሰድ የዘወትር ተግባሩ ሆኗል ብለዋል። 


''የጥፋት ቡድኑ በንጹሀን ላይ እያደረሰ ያለው ጥቃት በትእግስት የምናልፍበት ደረጃ ላይ አይደለንም'' ያሉት ደግሞ በወረዳው የሚኖሩት የቦረና አባገዳ ኩራ ጃርሶ ናቸው፡፡  

ህዝቡ ቡድኑን ለህግ አሳልፎ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ እንድሪስ የዴ በበኩላቸው ከሀይማኖት፤ ብሄርና ፖለቲካ ገለልተኛ ሆኖ ሀገር በሚጠብቅ መከላከያ ሠራዊት ላይ ህወሀት የፈጸመው ጥቃት ሀገር የማፍረስ እቅዱን በተግባር ያሳየበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሠራዊቱ ለህዝብና ለቅርስ ጥንቃቄ በማድረግ በጁንታው ላይ  የወሰደው የህግ ማስከበር ስራ የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከመንግስት ጎን በመቆም የጁንታውን ተላላኪ ኦነግ ሸኔን በማጋለጥ ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ታሪኩ አባይነህ በሰጡት አስተያየት ከሀዲዎች ሀገር ሲፈርስና ንጹሀን ሲጨፈጨፉ በዝምታ ማለፍ የታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል ብለዋል፡፡

አባገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለህወሀት ያቀረቡትን  የሰላም ጥሪ ውድቅ አድርጎ  ንጹሀንን ለሞትና ለስደት መዳረጉ የሚያሳዝን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለመከላከያ ሠራዊቱ ከወረዳው ህዝብ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የመንግስት ኮሚኔኬሽን ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ገልማ ሞሉ ናቸው፡፡

ህዝቡ አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅና የጥፋት ሀይሎችን በማጋለጥ ለሰራዊቱ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም