የፍጥነት መገደቢያና የጥፋተኛ አሽከርካሪዎች መረጃ ማቀናበሪያ ሶፍትዌር ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ዋለ

62

አዳማ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) የተሽከርካሪ የፍጥነት መገደብያና የጥፋተኛ አሽከርካሪዎች መረጃ ማቀናበሪያ ሶፍት ዌር ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ መዋሉን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ለተውጣጡ የዘርፉ የስራ ኅላፊዎችና ባለሙያዎች በሶፍትዌር አተገባበርና አጠቃቀም ዙሪያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያዘጋጀው የሁለት ቀን መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ለኢዜአ እንደገለፁት ባለስልጣኑ የትራንስፖርት ዘርፍን ለማዘመን የፍጥነት መገደቢያና የጥፉተኛ አሽከርካሪዎች መረጃ ማቀነባበሪያ ሶፍትዌር ማበልፀጉን ተናግረዋል።

"ባለፈው አመት ወደ ትግበራ የገባው ሶፍት ዌር ዘንድሮ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ እንዲውል ተደርጓል" ብለዋል።

በሀገሪቱ እየደረሰ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት  ከመቅጠፉ ባለፈ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአስር ሺህ የተሽክርካሪ አደጋ እየተከሰተ ያለውን 43 የሞት አደጋ ወደ አስር ዝቅ ለማድረግ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ሶፍት ዌሩ ስራ ላይ እንዲውል መደረጉን ነው የተናገሩት።

የህዝብ ፍላጎትን ባማከለ መልኩ የትራንስፖርት ሴክተሩን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ሶፍትዌሩ የትራንስፖርት ሴክተሩን ከማዘመን ባለፈ በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ ናቸው።

የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ አጠቃቀም የአሰራር ሥርዓት ትግበራን ወጥነት ባለው መልኩ ስራ ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያዎች ተገጥመው ስራ ላይ መዋላቸውንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም