ለአገር መከላከያ ሠራዊት 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እና የአይነት ድጋፍ ተበረከተ

82

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) ሶስት ክልሎች፣ ተቋማትና ማኅበራት ለአገር መከላከያ ሠራዊት 13 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር እና የአይነት ድጋፍ አበረከቱ።

የጋምቤላ ክልል 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ዞን 400 ሺህ ብር፣ 97 ሰንጋዎችና 102 በጎችን አበርክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 5 ሚሊዮን ብር፣ የፌዴራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ሠራተኞችም 313 ሺህ ብር ሰጥተዋል።

የጋሞ እናቶችም በጋሞ ሴት አደረጃጀት በኩል ጭኮ፣ ዳቦ ቆሎ፣ ቅቤና ማርን ጨምሮ የተለያየ አይነት ስንቅ ለሠራዊቱ አበርክተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ድጋፉን ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

የጋሞ እናቶችና የአሶሳ ዞን ነዋሪዎች ተወካዮች ለአገር ሠላምና ለሕዝብ ደህንነት ከሚሰራው መከላከያ ሠራዊት ጎን መቆማቸውን ለማረጋገጥ ድጋፉን ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

ድጋፉን የተቀበሉት የመከላከያ ሚኒስቴር የፋይናንስ ሥራ አመራር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ስለተደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠራዊቱን በመደገፍ ያደረገውን ርብርብ በየተሰማራባቸው መስኮች በመድገም ለአገር ሠላም መከበርና ዕድገት መረባረብ ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም