ኢትዮጵያ የህግ ማስከበሩን ተግባር ዓላማ ለማስረዳት ያከናወነችው ዲፕሎማሲ ውጤታማ ነበር ተባለ

79

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ዓላማ ለዓለም ለማሳወቅ የሰራችው ዲፕሎማሲ ስኬታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ህግ የማስከበር ተግባር በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ ተግባራት ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የፌዴራል መንግስት ሲያከናውን የነበረውን ህግ የማስከበር ተግባር ዓላማ ለዓለም መሪዎች ለማስረዳት የተሰሩ የዲፕሎማሲ ስራዎችን ዘርዝረዋል።

የህግ ማስከበር ተግባሩ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት ሳይደርስ መጠናቀቁንም ለተለያዩ አገራት የማስረዳት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

በአፍሪካና አውሮፓ በአካል፣ በበየነ መረብ፣ በስልክና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ዓላማውን የማስረዳት ስራ መከናወኑን ዘርዝረዋል።

በተለይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጎረቤትና በአውሮፓ አገሮች ባደረጉት ጉብኝት ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የመጡ ለውጦችን አስረድተዋል።

ለውጡን የህወሃት አመራሮች መጻረራቸውንና ወደ ለውጡ እንዲመለስ የፌዴራል መንግስት ሰፊ እድል እንደሰጣቸውም እንዲሁ።

የተሰጣቸውን እድል ከመጠቀም ይልቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በገንዘብና አደረጃጀት የሽብር ስራዎችን ሲደግፉ እንደነበር ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ህገ ወጥ ቡድኑ በሰሜን እዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት ህግ ለማስከበር የተወሰደው እርምጃ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በማስረዳት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።

ህግ የማስከበር ተግባሩ ንጹሃን ዜጎችን ሳይጎዳ መጠናቀቁን ከሩሲያ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይና ሌሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በስልክ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል።

በውይይቱም ድርድር ማድረግን በተመለከተ ህጋዊ ከሆነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እየተደረገ መሆኑንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የማስረዳት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አንስተዋል።

በሱዳን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዜጎችን ማንነት፣ ያሉበትን ሁኔታና ሌሎች መረጃዎችን እያጣራ በመሆኑ በአጭር ጊዜ እንደሚመለሱ አረጋግጠዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከሳዑዲ አረቢያ 325 ዜጎች ወደ አገራቸው ማስመለስ የተቻለ ሲሆን ከነዚህ መካከል 33ቱ ህጻናት፤ አብዛኞቹም ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመግለጫው በኢንቨስትመንት፣ ምጣኔ ሃብትና በሌሎችም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር በተከናወኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም