ለስልጣን ፍላጎት መሰረተ ልማቶችን ማፈራረስ ዜጎችን ወደ ድህነት በመመለስ የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል - ባለሙያዎች

48

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) ለቡድን የስልጣን ፍላጎት መሰረተ ልማቶችን ማፈራረስ ዜጎችን ወደ ድህነት በመመለስ የታሪክ ተወቃሽ የሚያደርግ ነው በማለት ባለሙያዎች ተናገሩ።

በአገሪቱ እየተገነቡ ያሉ መንገዶች ህዝቡ ዘመናትን ከተሻገረው የጉስቁልና ኑሮ ለመሻገር ከእለት ጉርሱ ቀንሶ የሚከናወኑ ናቸው። 

በኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የአገሪቱ በጀት ከፍተኛው ገንዘብ የሚመደበው ለመንገድ መሰረተ ልማት ነው። 

በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቷል።

በትግራይ ክልል በቅርቡ በተደረገው ህግ የማስከበር ዘመቻ የህወሃት አጥፊ ቡድን በአካባቢው የሚገኙ መሰረተ ልማቶች በማፈራረስ ታሪክ ይቅር የማይለው ተግባር ፈጽሟል።

የመንገድ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት ኢንጂነር አበበልኝ መኩሪያ የመንገድ ግንባታዎችን ማፍረስ የአካባቢውን ነዋሪ ከድህነት ለመውጣት የሚያደርገውን ትግል መገደብ ነው ይላሉ።

በኢትዮጵያ በአማካይ አንድ ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ለመገንባት 26 ሚሊዮን ብር ይጠይቃል።

በተጨማሪም አንድን አካባቢ ከሌላው የሚያገናኝ መንገድ ለመገንባት ከሶስት እስከ አራት ዓመት ይፈጃል ነው ያሉት።

በከፍተኛ ወጪ ረጅም ዓመታት ፈጅቶ የሚሰራን መንገድ ማፍረስ ከታሪክ ተወቃሽነት አያድንም ይላሉ።

"በተለይ አገር ሲያስተዳድር የነበረ፣ የአካባቢውን ችግር እፈታለሁ በሚል የሚታገል አካል ራሱ የገነባውን መንገድ የሚያፈርስ ደግሞ በጣም አሳዛኝ ነው" ብለዋል።

መንገድ ከዕለት ተዕለት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር በቀውስ ጊዜም ሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብም ጠቀሜታው የላቀ ነው።

‘’እኔ ከ20 ዓመት በላይ በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ያሳለፍኩ በመሆኔ የሰራሁት መንገድ ፈርሶ ሳየው ልጄን እንዳጣሁ ነው የተሰማኝ ‘’ ብለዋል ባለሙያው።

የአገሪቱ የመንገድ ሽፋን በጣም ዝቅተኛ ነው የሚሉት ባለሙያው የነገ ኑሯቸውን ለማሻሻል የመንገድ ግንባታ ጥያቄ ያላቸው ዜጎች በርካቶች መሆናቸውን ያነሳሉ።

የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ያለችውንም ማፍረስ ግን በህዝብ ሃብት መቀለድ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና አመራር መምህርና ተመራማሪ አለማየሁ ደበበ እንደሚሉት ደግሞ መሪ ወይም አመራር ለህዝብ እድገት እንጂ ጉስቁልና አይሰራም።

መንገድ ማፍረስ ደግሞ ዜጎችን ወደ ድህነት ማስገባት ነው ብለዋል።

ለህዝብ ተቆርቋሪ ነኝ በሚል የራሱን ፍላጎት ብቻ መሰረት አድርጎ የሚሰራ አካል በምንም መመዘኛ አገር ሊመራ እንደማይችል ህዝቡ ሊነቃ ይገባል ይላሉ። 

መሰረተ ልማት ማፍረስ አገር እንደማፍረስ ይቆጠራል ያሉት መምህሩ በቅርቡም በትግራይ ክልል የተደረገው ይህ ነው ብለዋል።

"የግል ፍላጎታችንን ወደ ጎን በመተው ለህዝብ የምንሰራበትን ጊዜ ማምጣት አለብን" ሲሉም ይመክራሉ።

''መሰረተ ልማት ሲፈርስ አፍራሹ ጥቂት ተጎጂው ብዙ ነው የሚሆነው ዜጎች ደግሞ ይህን ተገንዘበው መንገዳቸውን ከጥቃት መከላከል አለባቸው" ብለዋል።

የህወሃት የጥፋት ቡድን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በተለያዩ የመሰረተ ልማቶች ላይ ውድመት ማድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም