የተፈፀመብን ግፍ የሕግ ማስከበር እርምጃውን በቁጭትና በወኔ እንድናጠናቅቅ አድርጎናል - የሰሜን ዕዝ አባላት

84

አዲስ አበባ፣ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) በሠራዊቱ ላይ የተፈፀመው ግፍ የሕግ ማስከበር እርምጃውን በቁጭትና በወኔ ተነሳስተን በአጭር ጊዜ እንድናጠናቅቅ አድርጎናል ሲሉ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።

መንግስት በፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ ሲወስድ የነበረውን የሕግ ማስከበር እርምጃ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ወደ 'ወንጀለኞችን የማደንና የመልሶ ግንባታ ምዕራፍ' ተሸጋግሯል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ደግሞ የሕግ ማስከበር እርምጃው በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ታሪክ የሚዘክረው አኩሪ ገድል ፈጽመዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰሜን ዕዝ አባላት እንደሚሉት፤ ፅንፈኛው የህወሓት ቡድን ከኦነግ ሸኔ የጥፋት ክንፉ አባላት ጋር በመሆን ትግራይን ለዘመናት በጠበቁ የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ያልታሰበ ጥቃት ፈጽሟል።

ቡድኑ ጥቃቱን ድንገት በሌሊት ቢፈጽምም፤ የሠራዊቱ አባላት እጅ ከመስጠት ይልቅ ከፅንፈኛ ቡድኑ ታጣቂዎች ጋር በመፋለም የተለያዩ ስልታዊ አማራጮችን መተግበራቸውን ነው የሚገልጹት።

ጥቃቱንም አብረዋቸው የነበሩ ከሃዲ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከፍተኛ መኮንኖች ሲመሩት እንደነበረም ነው ያብራሩት።

ሠራዊቱ ያለ ምግብና ውሃ ራሱን ከተከላከለ በኋላ ያሉ ሜካናይዝድ መሳሪያዎችን በመያዝ ወደ ኤርትራ ስልታዊ ማፈግፈግ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

ነገር ግን ፅንፈኛው ቡድን ስልታቸው እውን እንዳይሆን መንገድ በማፍረስና ፈንጂ በማጥመድ ጭምር ያልተሳካ ሙከራ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህም ሳይበግረው ሜካናይዝድ የጦር መሳሪያዎችን ይዞ መውጣቱን ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱም "ሀገሬን ማዳን አለብኝ" በሚል ወኔ በአጭር ጊዜ በመቀናጀት ወደ መልሶ ማጥቃት መሸጋገሩን ነው የሚያወሱት።

በተወሰደው ማጥቃትም በአጭር ጊዜ ቡድኑ የዘረፋቸውን መሳሪያዎች ሳይጠቀምባቸው መልሶ መቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል።

የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን የመዋጋት ዝግጁነት ሳይኖራቸው "ልዩ ሃይል" ብሎ ያደራጃቸው ታጣቂዎችም የሠራዊቱን ጀግንነት መቋቋም እንዳልቻሉ አውስተዋል።

የሠራዊቱ አባላት አሁንም የሚጠበቅባቸውን ማንኛውንም አይነት ተልዕኮ በብቃት ለመፈፀም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የህወሓት ጁንታ በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ያደረሰው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም