የአማራ ክልል አቀፍ የመስኖ ልማት የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ

92

ባህርዳር ህዳር 25/2013 የ2013(ኢዜአ) የአማራ ክልል አቀፍ የመስኖ ልማት የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በደቡብ ጎንደር ዞን ደራ እና ፎገራ ወረዳዎች ዛሬ ተካሂዷል።

በመረሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት የተገኙት  የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ  እንደገለጹት በዓለም ላይ ያሉ ሃያላን ሀገራት የበላይነታቸውን ያረጋገጡት በገነቡት ጠንካራ ኢኮኖሚ  ነው።

የአማራ ህዝብ ጠንካራ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባለቤት እንዳይሆን የትህነግ  ቡድን ለዘመናት በጠላትነት ፈርጆ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።

ትህነግ በራሱ ጠብ አጫሪነት በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት በመፈጸም  በጀመረው ጦርነት ምክንያት በመላ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ተጋድሎ የሽንፈት ጽዋ መቅመሱ ለህዝብ ታላቅ ድል መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን  ላይ በህግ ማስከበር ዘመቻው የተገኘውን ድል ለማስቀጠል የሚቻለው በኢኮኖሚው መስክ የሚጠበቀውን ውጤት በማስመዝገብ መድገም ሲቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም መላ የክልሉ ህዝብ በየአካባቢው ያለውን ሁሉንም የውሃ አማራጮች በመጠቀም በመስኖ ልማት ስራዎች በመሳተፍ ከዝናብ ጠባቂነት የተላቀቀ  አኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት መስራት አለበት ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን  በበኩላቸው በዘንድሮ  የበጋ ወቅት በመጀመሪያው ዙር ከ248ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተዘሩ የአትክልት፣ የቅመማቅመም፣ የስራስርና ሌሎች ሰብሎችን ቀድሞ በማንሳት በ2ኛው ዙር ደግሞ 108ሺህ ሄክታር መሬት አልምቶ  አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋልው።

በበጋው  መስኖ ከሚለማው መሬትም 37 ሚሊየን ኩንታል በማምረት በአንበጣ መንጋ የሚቀንሰውን ምርት ለማካካስ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የመስኖ ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግም ዘመናዊ የውሃ ማጠጫ ቴክኖሎጂን፣ የምርጥ ዘር፣ ሌሎችም  ግብአቶችትና  አዳዲስ አሰራሮች ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የተያዘውን ግብ ለማሳካትም  እስከ ቀበሌ ያሉትን የግብርና ባለሙያዎች በማሰልጠን አዳዲስ እውቀትና ግንዛቤ በማያዝ ተልኳቸውን እንዲወጡ የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም