በአዳሚ ቱሉ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ7 ሰዎች ህይወት አለፈ

58

አዳማ ህዳር 25/2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የ7 ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽንናና ሚዲያ ሃላፊ ኮማንደር አስቻለው አለሙ ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው የደረሰው በአዳሚ ቱሉ ወረዳ ድሎ ሬጴ ቀበሌ ውስጥ ትናንት ማምሻውን  ነው።

በዚህም አሽከርካሪውን ጨምሮ የሰባት ሰዎች ህይወት ወደያውኑ ማለፉን አስታውቀዋል።

አደጋው የደረሰው ከቡታ ጅራ ወደ ባቱ እየተጓዘ ያለው ኮድ 3-41179 ኦሮ ሚኒባስ የህዝብ ማመላለሻ 16 ሰዎች  ጭኖ በፍጥነት ሲጓዝ በመገልበጡ መሆኑን ኮማንደር አስቻለው አስረድተዋል።

በአደጋው ህይወታቸው ካለፈ ሰዎች በተጨማሪ አምስት ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶ በአዳማ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከአደጋው አራት ህፃናት ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መትረፉቸውን ኮማንደር አስቻለው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም