በህግ ማስከበር ዘመቻው የተሳተፉ ጀግኖችን ገድል በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች እናስተዋውቃለን---የዘርፉ ተዋንያን

68

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ የተሳተፉ ጀግኖችን ገድል በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ለማስተዋወቅ ዝግጁ መሆናቸውን የዘርፉ ተዋንያን ገለጹ። 

''ጥበብ ለአገር ክብር'' በሚል ድጋፍ ለማሰባሰብ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተቋቋመው ኮሚቴ አባላት አርቲስት ደበበ እሸቱና አርቲስት ተስፋዬ ማሞ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አርቲስቶቹ የአገር ክብርና ኩራት በሆነው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን ሠራዊቱንም ሆነ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች እንዲደግፉ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር በትግራይ ክልል በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ የተሳተፉ ጀግኖች ታሪክ ተዘርዝሮ እንደማያልቅ አመልክተዋል።

ይህን ጀብዱ በተለይ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሥራዎቻቸው ሊዳስሱት ቢችሉ ሲሉም ማንሳታቸው ይታወቃል።

አርቲስት ተስፋዬ ማሞ እንደሚለው በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ የጥበብ ሥራዎች በየትኛውም አገር የተለመዱ ከመሆናቸው ባለፈ ሽሚያ ይበዛባቸዋል።

እስራኤል በኡጋንዳ የታገቱ ዜጎቿን ለማስለቀቅ በ90 ደቂቃ ያከናወነችውን ውጤታማ ዘመቻ ለማሳየት የተሰራውን ፊልም ለአብነት ጠቅሷል።

"የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ልዩ ኃይል አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በብቃት ያጠናቀቁት ህግ ማስከበር ዘመቻ በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተካተው መቅረብ አለባቸው" ብሏል።

እንዲህ አይነት እውነተኛ የጀግንነት ታሪኮችን በጥበብ ይዞ ማስቀረት ለባለሙያው ትልቅ ክብር እንደሆነም ነው የገለጸው።

አርቲስት ደበበ እሸቱ በበኩሉ "ኢትዮጵያን እስከዛሬ ያስቸግራት የነበረው የውጭ ጠላት ነበር" ብሏል።

ይህ ክስተት አዲስ ከመሆኑ አኳያ በጥበብ ሥራዎች ቢከተብ ለብዙዎች መማሪያ ይሆናል ብሏል።።

በአገሪቷ ወቅታዊ ነገር ሲከሰት በተደራጀ መልኩ በዘርፉ ሙያዊ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የኪነ ጥበብ ፋውንዴሽን ሊቋቋም ይገባልም ብለዋል አርቲስቶቹ።

ይህም በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ ለሚከሰቱ ችግሮች የተደራጀ ምላሽና ድጋፍ ማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም