የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ እየተሰራ ነው- ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ

110

አዲስ አበባ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ የህግ ማዕቀፎች ተግባራዊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ተናገሩ።

ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያ አካልጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽንና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።

በአገሪቱ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች መኖራቸውን ተናግረው ህጎቹን ተግባራዊ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። 

በቅርብ ጊዜ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በባለቤትነት የሚመራ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ እየሰራ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ዳይሬክቶሬቱ ሌሎች በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ህግም በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ህጉ የአካል ጉዳተኞችን ችግሮች በማቃለል እንዲሁም እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ሁሉን አቀፍና አስገዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።

ድህረ ኮቪድ-19 ምቹ መደላድል መፍጠር እንደ መንግሥት ያለብን ኅላፊነት ነው ያሉት ሚኒስትሯ በዘላቂነት አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም መንደፍ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አካልጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ እለቱ ሲከበር መንግስት አካልጉ ዳተኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች በሰራበት አጋጣሚ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በእለቱም ስምንት ሙዚቃዎችን ያካተተና በአካል ጉዳተኝነት ላይ የሚያጠነጥን የሙዚቃ አልበም በተለያዩ አርቲስቶች ተዘጋጅቶ ቀርቧል።

በዓለም ለ29ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረው የአካል ጉዳተኞች ቀን "አካል ጉዳተኞችን አካታች፣ ምቹና ዘላቂ የተሻለ ዓለምን በድህረ ኮቪድ-19 እንገንባ" በሚል መሪ ሐሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር በተለያዩ ኩነቶች ይከበራል።

በብሔራዊ ደረጃ ታህሳስ 17 እና 18 ቀን 2013 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ እንደሚከበር የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም