የሕወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ሰራዊትና በህዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ በጦር ወንጀል ሊጠየቅ ይገባል- ሜ/ጀነራል ጌታቸው ገዳሙ

62

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) የሕወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብና መከላከያ ሰራዊት ላይ በፈጸመው ግፍ በጦር ወንጀል ሊጠየቅ እንደሚገባ የቀድሞው ጦር ሰራዊት አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጀነራል ጌታቸው ገዳሙ ገለጹ።

ከ1946 ዓ.ም ጀምሮ ከእግረኛ ወታደር እስከ ሜጀር ጀኔራል ማዕረግ የደረሱት ሜጀር ጀኔራል ጌታቸው በ18ኛ ኮርስ ዕጩ መኮንን ሆነው ገነት ጦር ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል።

ከዚያ በኋላም በአሜሪካ የወታደራዊ ጥበብ ተምረው እስከ 1983 ዓ.ም ድረስ በጦሩ ውስጥ ከመድፈኛ ሻለቃ አዛዥነት እስከ የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ እንዲሁም በአንደኛ አብዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ ሆነው አገልግለዋል።

ከሁመራ ገስጥ ዘመቻ እስከ ዚያድ ባሬ ወረራ ካራማራ፣ ከባልታግ እስከ ቆሬና ቶጎ ውጫሌ ውጊያዎች አዝማች ነበሩ።

በማዕከላዊ ዕዝ የሰው ሀብት ሃላፊነት እንዲሁም በኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን የበረራ ደህነንት ጥበቃ ሃላፊ በመሆን በተለያዩ አገሮች ተዘዋውረው አገራቸውን አገልግለዋል።

እኒህ የቀደመ ታሪክ ያላቸው ወታደርና የታሪክ ፀሃፊ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሕወሃት ቡድን ለአገሩ አንድነትና ሉዓላዊት መስዋዕትነት ሲከፍል የቆየውን ጦር በመበተን ኢትዮጵያን ማፍረስ እንደጀመረ ያስታውሳሉ።

ህወሃት የመገንጠል እንጂ ኢትዮጵያዊ አስተሳስብ እንደሌለውም ገልጸዋል። በመሆኑም የሕወሃት ቡድን በቅርቡ በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ጥቃት ሲፈጠር ጀምሮ የነበረው ሊለወጥ የማይችል ባህሪው መገለጫ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ድርጊት 27 ዓመታት በስልጣን ቆይቶም ይህ ባህሪው እንዳልተለወጠ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

“አገሩን ለጠላት አሳልፎ ለመስጠት የቤቱን አጥር ለማፍረስ የሚፍጨረጨረው የህወሃት ቡድን በሰራው ወንጀል ልክ ተጠያቂ መሆን ይኖርበታል” ነው ያሉት።

ከመጀመሪያው ጀምሮ በሰራዊቱና በንጹሃን ላይ ለፈጸመው ግፍ፣ ወንጀሉ መታየት ያለበት በጦር ፍርድ ቤት ወይም በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም