በምዕራብ ጎንደር ዞን የአካባቢን ፀጋ መሰረት ያደረገ የስራ እድል እየተመቻቸ ነው

43

መተማ ህዳር 24 /2013 (ኢዜአ) የአካባቢውን የመልማት ፀጋ መሰረት በማድረግ ለወጣቶች የስራ እድል እየተመቻቸ መሆኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ገለጸ፡፡

በገጠርና ከተማ የእርሻ ልማት፣ እጣንና ሙጫ፣ መስኖ ልማት፣ አሳ ሃብት፣ አሸዋና ድንጋይ፣ ኢንቨስትመንት ቦታዎችና  የግንባታ  ዘርፎች በዞኑ በአካባቢ ፀጋነት ተመራጭ ተደርጎ  ወደ ስራ መገባቱን  የመምሪያ ሃላፊው አቶ መብራቱ አዲሱ ለኢዜአ ተናግረዋል።

እስካሁንም 3ሺህ ሄክታር በጣንና ሙጫ የተሸፈነ፣ 600 ሄክታር ለእርሻ ተስማሚ የሆነ፣ 10ሺህ መሬት ደግሞ የቆላ ስንዴን ጨምሮ በመስኖ የሚለማ መሬት መለየቱን አስረድተዋል።

በእነዚህ የአካባቢ ፀጋዎች በበጀት ዓመቱ ከ21ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች  የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ   እስካሁን  6ሺህ 880   ወጣቶች  ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደተመቻቸላቸው ገልጸዋል።

የተመቻቸላቸውም በ870 ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተው በከተማ ግብርና፣ ግንባታ ዘርፍ፣ እንስሳት  እርባታ፣ በአሸዋና ድንጋይ ማምረት መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በሚፈጠር የስራ እድል በአብዛኛው በጊዜያዊነት ስለነበር እንደገና ሥራ ፈላጊ  በመሆን ሲፈጠር የቆየውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  አብራርተዋል።

በመተማ ወረዳ ሽንፋ ከተማ 20 ሆነው በመደራጀት በአሽዋና ድንጋይ ማምረት ዘርፍ እንደተሰማሩ  የገለጸው ወጣት ከማል ዮሱፍ እንደተናገረው ከወዲሁ የተሻለ ገቢ ማግኘት በመጀመራቸው ተግተው እየሰሩ ነው።

ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ሥራ ከጀመሩ  ወዲህ 100ሺህ  የሚጠጋ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመው ተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር ጠይቀው የአሸዋና ድንጋይ መጫኛ ትራክተር  ለመግዛት ማቀዳቸውን ገልጿል።

በዚሁ ወረዳ ኩመር አፍጥጥ ቀበሌ በመስኖ ልማት በመሰማራት ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲምና ቃሪያ በማልማት ከሚገኙት መካከል ወጣት ሰሎሞን ጋሹ በበኩሉ የተሰጣቸውን መሬት በመስኖ እያለሙ  መሆናቸውን ተናግሯል።

አስር ወጣቶች ሆነው በመደራጀት ያለሙትን ቲማቲምና ቃሪያ በመሸጥ  ከ150 ሺህ ብር በላይ ገቢ  ማግኘታቸውን ጠቅሶ  አሁን ላይ በሁለተኛው ዙር መስኖ ሽንኩርት ለማልማት እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁሟል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት 16ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መመቻቸቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም