በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ዜጎች ኑሯቸው በዘላቂነት እንዲሻሻል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

68

ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ዜጎች በዘላቂነት ኑሮኣቸው እንዲሻሻል እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ የምግብ ዋስትና እና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ አስታወቀ።

የመዲናዋ የምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ ላለፉት አምስት አመታት ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስ እንዳሉት ባለፉት አምስት አመታት በከተማዋ በሴፍቲኔት ፕሮግራም ለበርካቶች የስራ እድል ተፈጥሯል፡፡

በተፈጠረው የስራ እድልም ለ415 ሺህ 923 የመዲናዋ ነዋሪዎች በተለያዩ የአካባቢ ልማት ስራዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በሂደቱ አስካሁን 349 ሺህ 375 ዜጎች በአካባቢ ልማት ስራዎች ሲታቀፉ 66 ሺህ 548 ወይም 16 በመቶው ደግሞ ቀጥታ ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በአካባቢ ልማት ስራ ላይ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ከሰሩ በኋላ ወደ ዘላቂና ተከታታይ የኑሮ ማሻሻያ ድጋፍ ፕሮግራም ይሸጋገራሉ ብለዋል።

በዚህ ፕሮግራም የምግብ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ አልባሳትና ሌሎችንም ጨምሮ በዘላቂነት ኑሯቸው የሚደጎም መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አረጋግጠዋል።

የፕሮግራሙን ተጠቃሚዎች በዘላቂነት ለመደገፍ የሚያስችል ተከታታይ ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮግራሙ ስልጠናን ከመስጠት ባሻገር ለመነሻ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግና ይህም በቤተሰብ ደረጃ ስራ ለማስጀመር የሚውል አንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም