የለውጥ አመራሩ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን የሚገነባው በተግባር ነው...አቶ ሽመልስ አብዲሳ

109

አዲስ አበባ፤ ህዳር 24/2013(ኢዜአ)የለውጥ አመራሩ እውነተኛ ፌዴራሊዝም እገነባለሁ ሲል በአፍ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ተግባር ነው ሲሉ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳትን አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

15ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ዛሬ የተለያዩ ተግባራትን በመከወነ ተከብሮ ውሏል።

“ህብረ-ብሔራዊ አንድነትና እኩልነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰንን ጨምሮ፣ የጋምቤላ ክልልና የደቡብ ህዝቦች ክልል አፈ ጉባዔዎች እንዲሁም የሲዳማ ክልል ልዑካን ቡድን በእንግድነት ታድመዋል።

በበዓሉ ላይ ለታዳሚዎቹ እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የክልሉ ምክርቤት አፈጉባዔ ሎሚ በዶ እንዳሉት መንግስት ህዝቡን በማስተባበር የጥፋት ቡድኑ ላይ ድል በተቀዳጀበት የሚከበር በመሆኑ በዓሉን የተለየ ያደርገዋል።

ለታዳሚዎቹ መልእክታቸውን ያስተላለፉት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው ከለውጡ በፊት የነበረው ፌዴራሊዝም "አንዱ የአገር ባለቤት ሌላው ዳር ተገፍቶ የነበረ የውሸት ፌዴራሊዝም ነው" ብለዋል።

የለውጥ አመራሩ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ግን ብዝሃነትና እኩልነትን ባማከለ እውነተኛ ፌዴራሊዝም በመገንባት ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።  

አምና ዘጠኝ ክልሎች ሆነን ያከበርነው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ በ10 ክልሎች መከበሩ ደግሞ እንደ አብነት የሚነሳ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ ከሃዲው ጁንታ በክህደት ተግባሩ ከ45 ዓመት በፊት ወደ ነበረበት ዋሻው ተቀብሮ ባለበት በአሁኑ ወቅት መከበሩ ደግሞ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል።

ክልላቸውን በእጅ አዙር በማስተዳደር ህዝብን ሲገድልና ሲተያስገድል የነበረው የህወሓት  የዘረፋ ቡድን አሁን ካለበት የሞት አፋፍ ላይ በቅርቡ ተለቅሞ ህግ ፊት የሚቀርብበት ጊዜ መሆኑን ያወሱት ደግሞ የበዓሉ የክብር እንግዳ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ናቸው።

በበዓሉ ኦሮሚያን ወክለው የብሔር ብሔረሰቦች የቁንጅና ውድደር ላይ የሚቀርቡት የኦሮሚያ ሶስት 'ሚሲ ዩኒቲ' አሸናፊዎች በክልሉ ፕሬዝዳንት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የብሔር ብሔረሰቦች ችቦም ከጋምቤላ ክልል ተወካይ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተሰጥቷል፤ ችቦው ተለኩሷል፣ የ15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል ኬክም ተቆርሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም