ኮሮናን በመከላከሉ ረገድ ያለው መዘናጋት አስጊ መሆኑ ጥንቃቄ ሊደርግ እንደሚገባ ተመለከተ

60

ባህርዳር ህዳር 24 / 2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት አስጊ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደርግ እንደሚገባ ተመለከተ። 

የክልሉ ኮሮና  መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ  ለጋዜጠኞች እንደገለጹት የቫይረሱ  ስርጭት በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በክልሉ እየጨመረ ይገኛል።

በሽታው በፈጠረው ስጋት ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ስራው ተገቢው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመካሄዳቸው ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲጀመር መደረጉን ጠቅሰዋል።

መማር ማስተማሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት መከናወን አለመከናወኑን ለማረጋገጥም ከትምህርት፣ ጤና፣ ቴክኒክና ሙያና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የመስክ ምልከታ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

በተደረገው የመስክ ምልከታም በሽታውን ለመከላከል የሚያግዙ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ፣ የቀረቡ የንጽህና መጠበቂያ ውሃ አገልግሎትን በአግባቡ ያለመጠቀም ችግር መስተዋሉን አስረድተዋል።

ችግሩ ከተማሪዎች በተጨማሪ በመምህራን በኩልም መታየቱን ገልጸው፤ በቀጣይ ይህንን ክፍተት ለማስተካከል  ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በማህበረሰቡ በኩል የታየው መዘናጋት በትምህርት ቤቶች ጭምር በስፋት እንዲስተዋል ማድረጉንም ጠቁመዋል።

በሽታው ከሃገሪቱ መጥፋቱ እስኪረጋገጥ ድረስ ህብረተሰቡም ሆነ ተማሪዎች ከመዘናጋት ተላቀው ርቀትን በመጠበቅ፣ ጭንብል በመጠቀምና  ንጽህናን በሚገባ በመጠበቅ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ አመልክተዋል።

መምህራንም ሆነ ወላጆች ተማሪዎች በተገቢው መንገድ ወረርሺኙን ለመከላከል የሚያስችሉ መመሪያዎችን እንዲተገብሩ በማገዝ የበኩላቸውን  እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ በክልሉ በበሽታው  ከተያዙ ከስድስት ሺህ  በላይ ሰዎች መካከል  108 ህይወታቸው ማለፉን  ዶክተር ሙሉነሽ  አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም