በጁንታው መወገድ ብሄር ብሄረሰቦች ግጭት ውስጥ የሚገቡበት ዘመን ያከትማል--የጅማ ከተማ አስተዳደር

73

ጅማ ህዳር 24/2013 (ኢዜአ) በህግ ማስከበር እርምጃው የጁንታው ቡድን መወገድን ተከትሎ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ግጭት ውስጥ የሚገቡበት ዘመን የሚያከትም መሆኑን የጅማ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ። 

15ኛውን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  ቀን በዓል ዛሬ በጅማ ከተማ ተከብሯል።

የጅማ ከተማ አፈ- ጉባኤ አቶ ሰለሞን ቀኖ በወቅቱ እንደገለጹት በሀገሪቱ ባለፉት አመታት እውነተኛ  ፌዴራሊዝም የሚመራ የፖለቲካ ኃይል ባለመኖሩ በርካታ ጥፋቶች ሲደርሱ ነበር።

"በአመታቱ ሲደርሱ ከነበሩ ጥፋቶች መካከል የብሄር ግጭት አንዱና ዋናው ነው" ብለዋል።

ሀገሪቱን በበላይነት ሲያስተዳድር በነበረው የጁንታው ቡድን በነበረው ህዝብን የመነጣጠል የሴራ ፖለቲካ ፍላጎት እውነተኛ ፌደራሊዝም ተግባራዊ ሳይደረግ በመቅረቱ ለብሄር ግጭት ምክንያት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል ።

"አሁን ላይ መንግስት በወሰደው ህግ የማስከበር እርመጃ ቡድኑ በመወገዱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እርስ በእርስ የሚጋጩበት ዘመን አብቅቷል" ብለዋል፡፡

የጅማ ከተማ ከንቲባ አቶ ቲጃኔ ናስር በበኩላቸው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀንና የህገ መንግስት ምስረታ የኢትዮጵዊያን ተጋድሎ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ይሁንና ባለፉት 27 አመት ህገ መንግስቱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን እኩል ያስተናገደ አልነበረም" ብለዋል፡፡

ህገ መንግስቱ ሁሉን ኢትዮጰያዊያን እኩል ባለማስተናገዱ ከተከሰቱ ጥፋቶች አንዱ በብሄሮች መካከል ግጭት እንዲኖር ማድረግ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

"በውጤቱም  የለውጥ ኃይሉ በህዝብ ግፊት ወደ ስልጣን በመምጣት ሀገራዊ ለውጥ እንዲያካሂድ አድርጓል" ብለዋል።

የለውጥ አመራሩ የህዝብ ፍላጎት የሆነው የብሄር ብሄረሰቦች እኩልነትና ብልጽግናን የማረጋገጥ ተግባር ስኬታማ እንዳይሆን በህወሓት በርካታ ተግዳሮቶች እንደተደረገበት ጠቅሰዋል፡፡

የለውጥ ኅይሉ ተግዳሮቶቹን ተቋቋሞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ተቋማዊ ግንባታና የልማት ስራዎችን በመለየት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተለይም በጀግናው መከላከያ ሰራዊታችን ውስጥ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰብ በማሳተፍ ኢትዮጵያዊ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እየተገነባና ውጤት እያመጣ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

"የለውጥ ኃይሉ ለዜጎችና ለሀገር ክብር የማይደራደር ቁርጠኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በመገንዘባቸው ድጋፍ እየሰጡ ይገኛሉ" ብለዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የተሳተፉ የጅማ ከተማ ነዋሪዎችም በኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት እንዲቆም ጠይቀዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ አበቡ ወራንኮ በሰጡት አስተያየት "ባለፉት አስራ አምስት አመት የተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የይስሙላና ህዝቦችን ለእርስ በእርስ የማጋጨት ሴራ የነበረበት ነው" ብለዋል፡፡

"ከዚህ በፊት በስመ ብሄር ብሄረሰቦች ሽፋን ለስልጣናቸውና ጥቅማቸው የቆሙ ቡድኖች ሰዎች እንዲገደሉና ንብረት እንዲወድም  ሲሰሩ ቆይተዋል" ያሉት ደግሞ አቶ አለሙ ሽፈራው ናቸው።

በሀገሪቱ ከዚህ በኋላ  የብሄር ብሄረሰቦች ግጭት እንዲቆም መንግስት ጠንካራ አቋም ይዞ እንዲሰራ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ።

በስነ ስርአቱ ላይ የበዓሉ ታዳሚዎች መከላከያ ሰራዊቱና ሌሎች የጸጥታ መዋቅር ለሀገር ህልውና ሲሉ በህወሓት ወታደራዊ ኃይል ላይ ለወሰዱት ውጤታማ እርምጃ እንዲሁም ብቁ አመራር ለሰጡት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ  አንድ ደቂቃ ቆመው በማጨብጨብ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የጅማ ከተማ ነዋሪዎች፣ የ12ኛ ክፍለጦር አባላት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል፣ የጅማ ከተማ ፖሊስና ሚሊሻ አባላት በስነ ስርዓቱ ላይ ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም